መንግሥት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ለሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ብቻ የነዳጅ ድጎማ እንደሚያደርግ አስታወቀ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሰኔ 7/2014 (ዋልታ) መንግሥት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ለሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ብቻ የነዳጅ ድጎማ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

እየተካሄደ ባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሀገራትን ወቅታዊ የግሽበት መጠን በመቶኛ በማስረዳት የኢትዮጵያ ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት 33 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

ነዳጅን በተመለከተ መንግሥት ከቀጣዩ ሐምሌ ወር ጀምሮ ለሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ብቻ ድጎማ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

የውጭ ምንዛሬን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብር ሕጋዊ ተመኑ መቀነሱ ለምጣኔ-ሀብቱ መጨመር አስተዋጽዖ አበርክቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመን መጠኑ ወይም የብር ምንዛሬው ከፍ ማለት ምጣኔ-ሀብቱን እንደሚጎዳ የዘርፉን ምሁራን ጠቅሰው ተናግረዋል።

የሕዝብ ጥቅምን ያስቀደመውን ኢንቨስትመንት በተመለከተ አፍሪካ ውስጥ የትኛውም መንግሥት የኢትዮጵያን ያህል ኢንቨስት እንደማያደርግ ገልጸው በዚህ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የነደፈችውን የብልጽግና የዕድገት እና ለውጥ በጽኑ መሠረት እየገነባች መሆኗን አመልክተዋል።

የዋጋ ግሽበት የሚጎዳው በዝቀተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን መሆኑን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ የምርት እጥረትና የፍላጎት ዕድገት፣ የገበያ ሥርዓት፣ የአምራችነት መስተጓጎል፣ የፋይናንስ አጠቃቀም ለግሽበቱ መንስኤዎች እንደሆኑ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የዳቦ ምርት በቀን 20 ሺሕ ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አሁን ላይ በሸገርና በብርሀን ዳቦ ቤቶች በቀን ከ2 ሚሊየን ዳቦ በላይ እንደሚመረትና 10 መለስተኛ ፋብሪካዎች በከተማ ደረጃ እየተቋቋሙ ጠቅሰዋል።

ፋብሪካዎቹ ሥራ ሲጀምሩ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዳቦ በቀን በአዲስ አበባ ይመረታል፤ ነገር ግን መጠኑ 10 ሚሊየን እስከሚደርስ ድረስ በቂ አይደለም ብለዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW