ታኅሣሥ 12/2014 (ዋልታ) በሱዳን በኩል የቅኝ ገዥዎችን የድንበር ጥያቄ መነሻ በማድረግ ተደጋጋሚ ትንኮሳ ቢፈፀምም ኢትዮጵያ በትዕግስት እያለፈችና ከወታደራዊ ምላሽ እንደተቆጠበች መንግሥት ገለፀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ለቱርኩ የዜና ወኪል አናዱሉ እንደገለጹት ለሽብር ቡድኑ የወገኑ አገራትና መገናኛ ብዙኃናቸው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ጥረት እያደረጉ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
ፖለቲካዊና መልከዓምድራዊ ፍላጎቶች በተለይም በአፍሪካ ከፍ ያሉ በመሆናቸው ጣልቃ ገብነትን ልናስወግድ አንችልም ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ኢትዮጵያ ቅኝ ባትገዛም እንኳን ለውጭ ሴራዎች ዛሬም ተጋላጭ እንደሆነች አንስተዋል፡፡
ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ የድንበሩ ጉዳይ ትናንት ወይም ዛሬ የተፈጠረ እንዳልሆነ አሳውቀዋል፡፡
ድንበሩ በራሱ ችግር ሳይሆን አንድ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሬድዋን ችግር የማይሆነው የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ በቦታው ስለነበሩ ነው ብለዋል፡፡
የድንበሩ ጉዳይ የመጣው ቅኝ ገዥዎች በስፍራው ከመጡ በኋላ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ በዚህም የአፍሪካ ችግሮች ሁሉ ከቅኝ ገዥዎች ዱካ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ነው ያሰመሩበት፡፡
ከሱዳን ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ገብተን አናውቅም ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱ ሕዝቦች አንድ ስለሆኑ ነው፤ የፖለቲካ ድንበሩ አርቴፊሻል ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ለወረራና ትንኮሳዎች በአሉታዊ መልኩ ምላሽ አልሰጠንም በማለትም አሁን ላይ በሱዳን የሽግግር መንግሥት በተለይም ከወታደራዊ ክንፉ በኩል ላሉ ትንኮሳዎች ምላሽ አልሰጠንም ምክንያቱም ማን እንደሚገፋቸው እናውቃለን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ ያሸንፋሉ፤ ሰላማችንንና ወንድማማችነታችንን እንጠብቃለን ሲሉም ተደምጠዋል፡፡