መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በቀዳሚነት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ይሰጣል – ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

መስከረም 28/2016 (አዲስ ዋልታ) መንግሥት በ2016 የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በቀዳሚነት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት እንደሚሰጥ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

6ኛው የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ መደበኛ የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል።

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመንግስት የ2015 አፈጻጸምና የ2016 ዓ.ም ዋና ዋና አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ንግግር አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ የሚያኮሩና ይበልጥ ለመስራት የሚያነሳሱ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶችን ማስመዝግቧን አንስተዋል።

መንግስት በ2016 ዓ.ም የፀጥታ ስጋት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሌብትና ብልሹ አሰራር እንዲሁም ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በዘላቂነት የሚያስቀር መፍትሄ በማምጣት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የዋጋ ንረትን ለማርገብ ቀዳሚው ትኩረት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን የገለጹ ፕሬዝዳንቷ ከዚህ ጋር ተያይዞም የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲ አፈጻጸምን ለመቃኘት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

በ2015 ዓ.ም 543 የእሁድ ገበያዎችን በተጨማሪነት በመክፈት ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡ ገበያዎችን 703 ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው በ2016 ዓ.ም ትኩረት ተደርጎበታል ነው ያሉት።

በየአካባቢው የዳቦ ፋብሪካዎችን በመክፈት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በኑሮ ውድነት ጫና ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ የማድረግ ስራ እንዲስፋፋ ይደረጋል ብለዋል።

ማዕድ ማጋራትና የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳትም በዜጎች የኑሮ መሻሻልና ድህነት ቅነሳ ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ በመሆኑ በዚህ ዓመትም ይበልጥ እንደሚሰራበት ነው ያነሱት።

በትምህርት ቤቶች የምገባ መርኃ ግብርም ከ6 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ድህነትን ከመቀነስ ባሻገር አምራች ዜጋ ለመፍጠርና ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል የሰብዓዊ ልማት ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።

በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በተከፈቱ የምገባ ማዕከላትም በርካታ ወገኖች እንዲመገቡ በማድረግ የኑሮ ጫናን የመቀነስ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው ይህም የሀገራችን ኢኮኖሚ ጠንካራነትና አካታችነት ያሳያል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።