ሚያዝያ 23/2013 (ዋልታ) – መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ፤ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ እንዲሁም በሁሉም አካባቢዎች ፀጥታና ሰላም የማስፈን ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ መነስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ለክርስትና ዕምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስተላልፈዋል፡፡
የትንሳዔ በዓል በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትርጉም እና ስፍራ ያለው ሲሆን ለዚህ ታላቅ ክብረ~በዓል በሰላም በመድረሳችሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ ነው ያስተላለፉት፡፡
በዚህ ጊዜ የሃገራችንን ልዑኣላዊነት አስጠብቆ ለማስቀጠል፤ የሰላም ዘብ ሆነን ለመዝለቅ እንዲሁም የተጋረጡብንን ፈተናዎች በድል ለመሻገር በፅናት ተደጋግፈን እና ተሳስበን በአንድነት የምንቆምበት ወሳኝ ወቅት ነው ብለዋል፡፡
በተለይ በየአከባቢው በተከሰቱ ግጭቶች እና ማንነትን መሰረት በማድረግ በተፈፀሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ በመሆኑ፤ ለነዚህ ወገኖች ትርጉም አዘል ድጋፍ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡
አክለውም ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻች በዕለት ደራሽ እና በመልሶ ማቋቋም የድጋፍ አግባብ በፍጥነት ለመድረስ በሃላፊነት ስሜት መረባረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡