ህግ ማስከበር ሂደቱ ኢትዮጵያ ሉአላዊት ሀገር መሆኗን ድጋሚ አለም እንዲያውቅ ያደረገ መሆኑ ተገለጸ

መከላከያ ሰራዊት በህግ ማስከበር ሂደቱ የተቀዳጀው ድል ኢትዮጵያ ሉአላዊት ሀገር መሆኗን ድጋሚ አለም እንዲያውቅ ያደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የፌዴራል ህብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ አመራሮችና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርኃግብር ያደረገ ሲሆን፣ ሰራተኞች 300 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ለሰራዊቱ ማሰባሰባቸውን እንዲሁም በሀገሪቱ ካሉ ህብረት ስራ ኤጀንሲዎች 100 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ እየሰራ መሆኑን የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ መሐሙድ ተናግረዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት በትራግይ ክልል ያከናወነው ህግ የማስከበር ተግባር ሀገርን ከጥፋት ቡድኖች ያዳነ፣ ኢትዮጵያ ሉአላዊት ሀገር መሆኗን ድጋሚ አለም እንዲያውቅ ያደረገና የሚያኮራ ስራ መሆኑንም አቶ አብዲ ገልጸዋል፡፡
ወጣቶች ከዚህ ቀደም የእኩይ አላማ አስፈፃሚዎች መሳሪያ ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አብዲ፣ አሁን ላይ ወጣቶችን ለሀገር ሰላምና እድገት እንዲሁም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለዋልታ የሰጡት የኤጀንሲው ሰራተኞች በበኩላቸው፣ መንግስት የጀመረውን የህግ ማስከበር ሂደት በማስቀጠል የጁንታው ቡድንን ለህግ ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የጁንታው ቡድን በሀገር ክህደት፣ ንብረት ውድመት እና በዘር ጭፍጨፋ ሊጠየቅ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
(በሳራ ስዩም)