ሙስናን የሚታገል ዜጋ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ሰኔ 4/2014 (ዋልታ) ሙስናን በትብብር እና በአንድነት መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፍትህ ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በሙስና ወንጀል ሕግ የሙስና ወንጀል ምርመራ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት እና ለዐቃቢያኔ ሕግ በሚዛን አማን ከተማ ስልጠና እየሠጠ ይገኛል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ተክሌ በዛብህ የሙስና ወንጀል በአደባባይ የሚፈጸም ሳይሆን ቀስ በቀስ ሀገርና ሕዝብን የሚጎዳ ካንስር መሆኑን ገልጸው ለሀገር የሚቆረቆር እና ለፍትህ መስፈን የሚጨነቅ ትውልድ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።

የሙስና ወንጀል ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሚዛን ከማዛባት ባሻገር የሰብአዊ መብት ጥሰት ያስከትላል ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት በፍትህ ሥርዓት ውስጥ ሲታይ የነበረው የተንዛዛ የዳኝነት ሥርዓት ለወንጀል ድርጊቱ መስፋት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል።

በመሆኑም ቀልጣፋ እና ፈጣን የዳኝነት ሥርዓትን በመዘርጋት የሙስና ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ገነት መንገሻ በበኩላቸው ፈጣንና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የፍትህ ሥርዓቱን ሚዛን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሀገሪቱ የያዘችውን የዕድገትና ብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ የሙስና ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር ይገባል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር የኅብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ምክትል አፈ ጉባኤዋ አዲሱን ክልል መልካም አስተዳደር የሰፈነበትና ከሙስና የጸዳ ለማድረግ በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ ኅብረተሰቡን ማገልገል ከፍትህ ተቋማት ይገባል ብለዋል።
በሚዛን አማን ከተማ ለአቃቢያኔ ሕግ ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።