ሚኒስቴሩ አዲስ የአምስት ዓመት የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ሪፎርም ስትራቴጅክ ዕቅድ ይፋ አደረገ

የገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

ጥቅምት 26/2016 (አዲስ ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስቴር ከ2016-2020  ባሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ሪፎርም ስትራቴጅክ ዕቅድ ዛሬ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ አድርጓል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታኢዮብ ተካልኝ  (ዶ/ር) ስትራቴጅክ ዕቅዱን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀው መድረክ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ውጤታማ የፋይናንስ አስተዳደር ያለውን  ጠቀሜታ በውል በመረዳትና ነባሩን ስትራቴጂ በጥልቀትና በስፋት በመገምገም ሚኒስቴሩ አዲሱን የሪፎርም ስትራቴጂ ዕቅድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ይህ የሪፎርም ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ መሆን የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደሩን ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ በማሻሻል መንግስት ለዜጎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ ያለውን ቁርጠኝነት በግልጽ ያመላክታልም ብለዋል፡፡

አዲሱ የሪፎርም ስትራቴጅ ተግባራዊ ሆኖ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው በባለድርሻ አካላት መካከል በሚኖረው የጋራ ጥረትና መደጋገፍ እንደሆነ ጠቅሰው ተጠያቂነትና ግልጽነት የሰፈነበት ውጤታማ የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደርን በጋራ አውን ለማድረግ በትብብር መንፈስ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የመንግስት ፋይናንስ ማሻሻያ ዲቪዥን ኃላፊ የሆኑት  ዳዊት ሽመልስ በበኩላቸው አዲሱ የአምስት ዓመት የመንግስት የሪፎርም ስትራቴጂክ ሰነድ በውስጡ የያዛቸውን ቁልፍ ዓላማዎች፣ የትግበራ ሂደት እና ውጤቶችን በዝርዝር ለወርክሾፑ ተሳታፊዎች ገለጻ ማድረጋቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡