ሚኒስቴሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን ገለጸ

መስከረም 6/2015 (ዋልታ) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን እና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በዚህም የታክስ ማሻሻያ ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ እንደሚደረጉ ታውቋል፡፡

የታክስ ማሻሻያው ዓላማ እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር በፖሊሲ ማዕቀፍ ከአካባቢ ደኅንነት ጋር የሚስማማ ለማድረግ፣ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል፣ በአየር ንብረትና በብዝኃ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ የማያሳርፍ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአግባቡ የሚጠቀም የመጓጓዣ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ ለማስቻል ያለመ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በታክስ ማሻሻያው መሰረት የኤሌክትሪክ የቤት ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ መደረጉ ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም በከፊል ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ አምስት በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን÷ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተወስኗል፡፡