ሚኒስቴሩ 30 ቢሊየን ብር መድቦ የግብርና ግብዓቶች እያቀረበ መሆኑን አስታወቀ

የግብርና ሚኒስቴር
መጋቢት 21/2013 (ዋልታ) – በዘንድሮው ዓመት 30 ቢሊየን ብር መድቦ የግብርና ግብዓቶችን በሚፈለገው ደረጃ እያቀረበ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓትና ገቢ ዳይሬክተር መንግሥቱ ተስፋ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ በዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ፣ የኬሚካል፣ የምርጥ ዘርና የአሲዳማ አፈር ማከሚያ ኖራ ግብዓቶች በታቀደውና በሚፈለገው ደረጃ እየቀረቡ ነው።
ለዚህም ባለፈው ዓመት የነበሩ ክፍተቶችን ቀደም ብሎ በመለየት የአርሶ አደሩን ፍላጎት በማሰባሰብ እንዴት፣ መቼና በምን መንገድ መቅረብ እንዳለባቸው እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት የአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት የሚያሳየው 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ወደ ተለያዩ ክልሎች የተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑን ጠቁመዋል።
እስከ መጋቢት 16 ድረስ 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ ደርሷል።
እስካሁን ወደ ሀገር ገብቶ የተጓጓዘው 7 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ነው ብለዋል።
ከባለፈው በጀት ዓመት ከተረፈው ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ጋር ተደምሮ 9 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ መኖሩን ገልፀዋል።
የህብረት ሥራ ማህበራት ቀበሌ ድረስ የተደራጁ በመሆናቸው ስርጭቱ በነሱ በኩል እየተካሄደ ነው ያሉት አቶ መንግሥቱ፣ እስካሁን ወደ ህብረት ሥራ ማህበራቱ የደረሰው የአፈር ማዳበሪያ 5 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ነው ብለዋል።
ከተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 64 በመቶ በህብረት ሥራ ማህበራቱ በኩል መሆኑን አመልክተው፣ እስካሁን በአርሶ አደሩ እጅ የገባው 987 ሺህ 694 ኩንታል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው ዓለም አቀፍ ግዥ ተፈፅሞ፣ በባህር ላይ ተጓጉዞ፣ ጅቡቲ ወደብ ላይ ተራግፎ፣ በየብስ ተጓጉዞ በመሆኑ አርሶ አደሩ እጅ የሚደርሰው ረጅም ሂደቶችን እና ጊዜ ወስዶ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በጥናት በመታገዝ ወደ ሥራ በመገባቱ የዘንድሮው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በአቅርቦትና ስርጭቱ በጣም ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነው ብለዋል።
ሂደቱ ቀድሞ መጀመሩ አርሶ አደሩ በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ይደርስበት የነበረውን መጉላላት በማስቀረት ሰብሉን በአግባቡ እንዲዘራ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያደርገው አመልክተዋል።
1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ይቀርባል ያሉት አቶ መንግሥቱ፣ ምርጥ ዘሩ ከውጭ የሚገባ ሳይሆን በሀገር ውስጥ ተመርቶ የሚቀርብ እንደሆነ አስታውቀዋል።
እስካሁን 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ምርጥ ዘር ቢሰበሰብም ለምርጥ ዘርነት የሚያስፈልገውን መስፈርት ስለማያሟላ በማሽን ተበጥሮ እና በባለሙያ ተለይቶ የተረጋገጠ 312 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።
ያለፈው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት 14 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የነበረ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ደግሞ ወደ 18 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል። የምርጥ ዘር ፍላጎቱም በተመሳሳይ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ወደ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል አድጓል።
ለምርትና ምርታማነት ዕድገት ተፅዕኖ ያላቸው እንደ አንበጣ፣ ግሪሳ ወፍና ሌሎች አእዋፋትንና ነፍሳትን ለመከላከል የሚያስችል በቂ የኬሚካል አቅርቦት እንዲኖር እየተሰራ ነው። የአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሊትር የኬሚካል ክምችት አለ። ተጨማሪ አቅርቦት እንዲኖርም ግዥ ለማካሄድ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛው የፌስቡክ ገፃችን
https://www.facebook.com/waltainfo
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛው የትዊተር ገፃችን
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!