ሚኒስቴሩ 33 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የወተት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን ለክልሎች በድጋፍ አበረከተ

ነሐሴ 1/2015 (አዲስ ዋልታ) የግብርና ሚኒስቴር 33 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ሰባት የወተት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን ለክልሎች በድጋፍ ማበርከቱ ተገለጸ።

ተሽከርካሪዎቹ ከዓለም ባንክ በድጋፍ የተገኙ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በተሽከርካሪዎች ቁልፍ ርክክብ ላይ ክልሎች የተረከቧቸውን ተሽከርካሪዎች በቅንጅትና በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል እንዳለባቸው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ተሽከርካሪዎቹ እያንዳንዳቸው 10 ሺ ሊትር ወተት ማጓጓዝ የሚችሉ ሲሆን በእንስሳትና ዓሣ ሃብት ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት በኩል የተገዙ ናቸው ተብሏል።

ተሽከርካሪዎቹ በድጋፍ የተበረከቱት ለኦሮሚያ ለአማራ ለደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እንዲሁም ለሲዳማ ክልሎች መሆኑ ታውቋል።

ድጋፉ የተደረገላቸው የክልል ቢሮ ተወካዮች በበኩላቸው ድጋፉ ከምርት በኋላ የሚጋጥመውን የወተት ብልሽት ከመቀነሱም በላይ የተመረተውን ወተት በቀጥታ ለገበያ ለማቅረብ ያግዛል ብለዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ወተት በስፋት የሚያመርቱ አካባቢዎች ላይ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረጉም ተጠቁሟል።
ውጤቱ የተገኘው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም በመቻሉ እንደሆነም ተመላክቷል።

በአማረ ደገፉ