ምርጫ ላይ ብቻ የሚሰራ አዲስ ምርመራ ዴስክ ተቋቁሟል – የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች ላይ ብቻ የሚሰራ አዲስ የምርጫ ምርመራ ዴስክ ማቋቋሙን አስታወቀ።

ፖሊስ ገለልተኛ በሆነ መልኩ መጪው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲከናወን ሃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑም ተገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተዘጋጀው ‘አዲስ ወግ’ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ፖሊስ በምርጫው ላይ ያለውን ዝግጁነት በሚመለከት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ በመልዕክታቸው “ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ እንደአገር በፖለቲካ ለውጥ ውስጥ ሆና የምታከናውነው በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል” ብለዋል።

መንግስት ዜጎች ያለምንም ተጽዕኖና ወከባ የፈለጉትን ፓርቲ የሚመርጡበት ምቹ መደላድል በመፍጠር ረገድ ቁርጠኛ አቋም መያዙንም ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር ፖሊስ ገለልተኛ ሆኖ ምርጫው በሰላም እንዲከናወን ሃላፊነቱን ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጉን አንስተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ምርጫውን በሚመለከት ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖችና ሌሎች ከሚለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ችግሮች ከዚህ ቀደም በመደበኛ የህግ ጥሰቶች ሲስተናገዱ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ምርጫን ብቻ የሚመለከት ገለልተኛ የምርጫ ምርመራ ዴስክ መቋቋሙን ገልጸው፤ ዴስኩ ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ አሰራር እንደሚመራ አብራርተዋል።

በተጨማሪ ፍርድ ቤቶችና አቃቤ ህግ የምርጫ ጉዳዮች ብቻ የሚስተናገዱበት አሰራር መዘርጋታቸው የዘንድሮውን ምርጫ ካለፉት አምስት ምርጫዎች ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ምርጫው በሰላም እንዲከናወን የሚሰማሩ የፖሊስ አባላት ከምርጫ ጋር የተያያዙ የስነ-ምግባር ስልጠናዎች እየተሰጣቸው መሆኑንም የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም፤ “ምርጫው ላይ የሚሰማሩ የፖሊስ አባላት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ይደረግባቸዋል” ብለዋል።

ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ ለሚሰማሩ የፖሊስ አባላት ልዩ መታወቂያ እንደሚዘጋጅላቸው  መገለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።