ምርጫ ቦርድ በእጩዎች ምዝገባ ወቅት 500 አቤቱታዎች መቅረቡን አስታወቀ

መጋቢት 08/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በእጩዎች ምዝገባ ወቅት 500 አቤቱታዎች ለቦርዱ መቅረቡን አስታወቀ፡፡

ቦርዱ በምርጫ ምዝገባ ወቅት የደረሱትን አቤቱታዎችና የተሰጡ መፍትሄዎች እና የምርጫ ቅስቀሳ በምን መልኩ መከናወን አለበት በሚለው ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተወያየ ይገኛል።

ለምርጫ ቦርድ ከቀረቡለት 500 አቤቱታዎች መካከል የተመዘገቡ እጩዎች ዝውውርና ስረዛ ጥያቄ፣ በፀጥታ ችግር ምክንያት በተቀያሪ ምርጫ ክልል የመመዝገብ ፍቃድ፣ የእጩዎች መታሰርና የምርጫ ክልል ቢሮ መዘጋት ጋር የታያዙ ጥያቄዎች ይገኙበታል ተብሏል።

ከአባላት መታሰርና ቢሮ መዘጋት ጋር በተያያዘ ግን ከቦርዱ አቅም በላይ በመሆኑ መፍትሔ አለመሰጠቱን አስታውቋል። ከዚህ ውጪ ያሉ አቤቱታዎች ግን ምላሽ ማግኘታቸውን ጠቁሟል።

በእጪዎች ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ይደርሳል፣ እጩዎቻችን በፀጥታ ምክንያት ማስመዝገብ አልቻልንም ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጥያቄያቸውን በውይይት መድረክ ላይ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ የካቲት 30/2013 ዓ.ም መጠናቀቁን መግለፁ ይታወሳል።

(በትዕግስት ዘላለም)