ምርጫ ቦርድ የመራጮች መመዝገቢያ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ክልሎች ማሰራጨት ጀመረ

መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ የሚከናወንባቸውን ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ክልሎች ማሰራጨት መጀመሩን ገለጸ።

ምርጫ ቦርድ ከትናንት መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ የሚከናወንባቸውን ቁሳቁስ የያዙ ሠማያዊ ሳጥኖችን ማጓጓዝ ጀምሯል።

በዚሁ መሰረት ለ49ሺህ 407 የምርጫ ጣቢያዎች ለእያንዳንዳቸው የመራጮች ምዝገባ የሚከናወንባቸውን ቁሳቁስ የያዘ አንድ ሠማያዊ ሳጥን እንዲዳረስ ስርጭት መጀመሩ ተገልጿል።

በሠማያዊው ሳጥን ውስጥ ዘጠኝ ዓይነት የመራጮች ምዝገባ ማከናወኛ ቁሳቁስ እንደሚገኙበት የገለጸው ቦርዱ፣ የመራጮች ምዝገባ ካርድ፣ የጽሕፈት መሣሪያ ዕቃዎች፣ በምርጫ ወቅት የሚጠቅሙ ቅፆች፣ መመሪያዎች፣ ፖስተሮችና የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁስ እንደሆኑ ተጠቁሟል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚከናወነው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የኦሮሚያ፣ የሱማሌና የአፋር ክልሎች የምርጫ ምዝገባ ቁሳቁስ የተዘጋጁት በየቋንቋቸው ሲሆን፣ የተቀሩት ክልሎች በአማርኛ ተዘጋጅቶላቸዋልም ነው የተባለው።

የመራጮች ምዝገባ የሚከናወንበት ሠማያዊ ሳጥን በእያንዳንዱ ክልልና የምርጫ ጣቢያ እስኪደርስ ምስጢሩ የተጠበቀና በፀጥታ ኃይሎች እጀባ የሚጓጓዝ መሆኑም ተገልጿል።

6ኛው አገራዊ ምርጫ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከናወን ሲሆን፣ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ምርጫው ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚከናወን የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል።

በአገር አቀፍ ደረጃ 673 የምርጫ ክልሎች እና 49 ሺህ 407 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙም የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።