ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በማከናወን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያስገቡ አሳሰበ

የካቲት 9/2014 (ዋልታ) የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በማከናወንና አስፈላጊ የሰነድ ማሻሻያዎችን በማድረግ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያስገቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ፡፡

ምርጫ ቦርዱ ኅዳር 23 ቀን 2014 ከፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር በአዋጅ ቁጥር 1162/11 እና በመመሪያ ቁጥር 3/2011 መሠረት ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ  እንዲያካሂዱና የሰነድ ማሻሻያ እንዲያደርጉ የተገለፀላቸው ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን አጠናቀው ባለማቅረባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በአንድ ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ እና ለቦርዱ እንዲያስገቡ መወሰኑ በምክክሩ ወቅት ለፓርቲዎች መገለጹን አስታውሷል።

በዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ መወሰኑን ተከትሎ ከታች ስማቸው የተዘረዘረላቸው ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በማከናወን እንዲሁም አስፈላጊ የሰነድ ማሻሻያዎችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በማድረግ እንዲያስገቡ ምርጫ ቦርድ አሳስቧል።

አገራዊ ፓርቲዎች

  1. የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ
  2. የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ
  3. የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ
  4. ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ
  5. የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ
  6. አዲስ ትውልድ ፓርቲ
  7. የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት
  8. የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር
  9. ብልፅግና ፓርቲ
  10. የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ
  11. የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
  12. ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
  13. የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ

ክልላዊ ፓርቲዎች

  1. የሲዳማ አርነት ንቅናቄ
  2. ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ
  3. የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ
  4. ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
  5. ኅዳሴ ፓርቲ
  6. የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
  7. የአፋር ሕዝቦች ፍትሐዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ
  8. የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ
  9. ቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ
  10. ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ ሉዓላዊነት
  11. የአርጎባ ብሔረ ሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
  12. የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
  13. የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡