ምክር ቤቱ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ለቋሚ ኮሚቴ መራ


መጋቢት 10/2016 (አዲስ ዋልታ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ለቋሚ ኮሚቴ መራ።

6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ወደ ሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ከዚህ ቀደም አዋጁ ለልማት ተነሺዎች ከሚከፈለው የካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የመሰረተ ልማት ገንቢው ተቋም ካሳ እንዲፈፅም፣ የወሰን ማስከበር ስራዎችን እንዲያከናውን እንዲሁም መሰረተ ልማቱንም እንዲገነባ ማድረጉ አላስፈላጊ ጫና እና የጊዜ ብክነት እየፈጠር መገኘቱም ተመላክቷል።

በመሆኑም ለሚከናወኑ መሰረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎቶች ማስፋፊያ በሚሆንበት ጊዜ ንብረት የመገመት፣ የመክፈልና የማስነሳት ስራ ሙሉ በሙሉ ለክልልና ከተማ አስተዳደሮች እንዲከወኑ ለማስቻል የአዋጅ ቁጥር 1161/2011 የተወሰኑ ድንጋጌዎችን ማሻሻል ስለማስፈለጉም ተገልጿል።

በዚህም አዋጅ ቁጥር 12/2016 በሚል ለከተማ መሰረተ ልማትና ለትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት የ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤም መርምሮ አፅድቋል።

በታምራት ደለሊ