የወሊድ መጠን በቀነሰባት ቻይና የተጋቢዎች ቁጥር በ9 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨመረ


መጋቢት 10/2016 (አዲስ ዋልታ) የወሊድ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በቀነሰባት ቻይና ለመጋባት የወሰኑ ጥንዶች ቁጥር ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ።

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት 2023 በቻይና 7 ነጥብ 68 ሚሊዮን አዳዲስ ተጋቢ ጥንዶች የነበሩ ሲሆን ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ12 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን የአገሪቱ የሲቪል ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ሚኒስቴሩ በፈረንጆቹ 2023 የተመዘገቡ አዳዲስ ተጋቢዎች ከ2022 ጋር ሲነጻጸር በ845 ሺሕ የሚበልጥ መሆኑንም አስታውቋል።

የቻይና የህዝብ ቁጥር በዝቅተኛ የወሊድ መጠን እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሞት ምክንያት ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የ2023 ሪፖርት አመላክቷል።

በአገሪቱ ውስጥ ብዙዎች በኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ምክንያት ላጤ ሆነው ለመቆየት መወሰናቸው እና ወጣት ሴቶች አገሪቷ ያሻሻለቻቸው የንብረት ሕጎች ለወንዶች ባለቤትነት ይወግናሉ በሚል ስጋት የጋብቻ መጠን አነስተኛ ሆኖ ቆይቷል።

የቅርብ ጊዜ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በፈረንጆቹ 2023 ለፍቺ የሚያመለክቱ ጥንዶች ቁጥር ጨምሯል። በዚህም በድምሩ 2 ነጥብ 59 ሚሊዮን ጥንዶች ለፍቺ መመዝገባቸውን ነው መረጃው የሚያሳው።

በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከጠቅላላው የአሜሪካ ህዝብ ጋር በሚመጣጠን መልኩ 300 ሚሊዮን ቻይናዊያን ጡረታ ይወጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ቻይና የሕዝብ ብዛትን ለመቆጣጠር ለረጀም ዘመናት የአንድ ልጅ ፖሊሲ ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች።

በዚህም ከፍተኛ በሆነ መልኩ የወሊድ መጠን መቀነሱን ተከትሎ የቻይና መንግሥት ጋብቻ እና የወሊድ ምጣኔ የተሳሰሩ በመሆናቸው የወሊድ መጠኑን ለመጨመር ፖሊሲውን አስተካክሎ ጋብቻን ያበረታታል።

በ2023 በቻይና የተጋቡ ጥንዶች ቁጥር በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ የሚባል ጭማሪ እንዳሳየ መገለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።

የቻይና መንግሥት ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚመጡ ወጭዎችን በመቀነስ እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የወሊድ ምጣኔን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝም ታውቋል።

ቻይና ከአንድ ልጅ ፖሊሲ ወጥታ በፈረንጆቹ 2015 ያጸደቀችው ተጋቢዎች ከሁለት በላይ ልጆች እንዳይወልዱ የሚያግደውን የቤተሰብ ህግ በማሻሻል በ2021 እስከ ሦስት ልጆች እንዲወልዱ መፍቀዷ ይታወሳል።