ምክር ቤቱ አሸባሪው ሸኔ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በጽኑ አወገዘ

ሰኔ 24/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ እና በሌሎች አካባቢዎችም በአሸባሪው ሸኔ እና ሌሎች መሰል ተላላኪ ጽንፈኛ ኃይሎች አማካኝነት፣ በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ በጽኑ አውግዟል፡፡

ምክር ቤቱ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሀገሪቱን ፀጥታ መዋቅር ከሚመሩ እና ከምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በስፋት ተወያይቷል፡፡

በውይይቱም ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ እና በሌሎች አካባቢዎችም በአሸባሪው ሸኔ እና ሌሎች መሰል ተላላኪ ጽንፈኛ ኃይሎች አማካኝነት፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ በጽኑ አውግዟል፡፡

በአንጻሩ መንግሥት የጀመረውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥልም በአጽንዖት አሳስቧል፡፡

በቅርቡ በተለያዩ የሀገሪቱ ስፍራዎች ማለትም በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ በደቡብ እና በሌሎችም አካባቢዎች ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተመላክቷል፡፡

ከሞት የተረፉትም ተፈናቅለው ለአካል እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል ሀብት ንብረትም ወድሟል ያለው ምክር ቤቱ ይህንን ዕኩይ ተግባር ምክር ቤቱ በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የምክር ቤቱ አባላት የየራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በምክክር መድረኩ አረጋግጠዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቀጣይ ትኩረት በሚፈልጉ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆነው ችግሩን ለመፍታት እንደሚሠሩ ገልጸው በአሁኑ ጊዜ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በአንድነት ቆመን መሻገር አለብን ብለዋል፡፡

ለሕዝባችን ኅልውና ቀን እና ማታ ከሚለፉ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የሚሠሩ ተግባራትን በተመለከተም ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ከሌሎች የመንግሥት አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከውስጥ እና ከውጭ ኃይሎች የተጋረጠብንን የኅልውና ጥያቄ ለመመለስ በመንግሥት በኩል የተያዘውን የለውጥ መንገድ ማገዝ እንደሚገባም አስምረውበታል።

ለተግባራዊነቱም በትጋት እንደሚረባረቡ የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ከምርክ ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW