ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ከህፃናት ጋር በመሆን ችግኝ ተከሉ

ሰኔ 26/2013 (ዋልታ) – “ኑ አዲስ አበባን እናልብሳት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ከህፃናት ጋር በመሆን ችግኝ ተክለዋል፡፡

የችግኝ ተከላው የነገ ሃገር ተረካቢ የሆኑ ህፃናት ለምንፈልጋት ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ከህፃናት ጋር የሚደረገው የችግኝ ተከላ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ለመሸፈን በምናደርገው ጥረት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ የሚያግዝ እንደሆነም ነው ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ የተናገሩት፡፡

በችግኝ ተከላው ላይ  የተሳተፉት  ህፃናት  ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ለአካባቢ አረንጓዴና ለአየር ንብረት ምቹነት የችግኝ ተከላው አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በከተማዋ የሚተከሉ ችግኞችን እንዲፀድቁና አዲስ አበባን እንደስሟ አበባ  እንድትሆን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉ ህፃናት ጠቁመዋል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ 8 መቶ ሺህ ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ነው፡፡

(በምንይሉ ደስይበለው)