ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከንግድ ማህበረሰብና ባለሀብቶች ጋር ተወያዩ


ሐምሌ 02/2013 (ዋልታ) –
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲሰ አበባ ከሚገኙ የንግድ ማህበረሰብ እና ባለሀብቶች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ አየተወያዩ ነው።
በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ በዲፕሎማሲ ሂደቶች እና ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ በሚመለከት ነው ውይይቱ እየተካሄደ የሚገኘው።
ከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት 500 ሚሊየን ብር ድጋፍ በማድረግ ለመከላከያ ሰራዊት ደጀን መሆኑን ባሳየበት መድረክ ላይ ተጨማሪ 2 ሚሊየን ብር ከማህበረሰቡ ለመሰብሰብ ቃል ገብቶ ነበር።
በዚሁም መሰረት ከንግድ ማህበረሰብ እና ከባለሀብቱ ጋር በመወያየት ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እያሰባሰበ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይቀዛቀዝ የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ ባለሀብቱ የበኩሉን አስተዋፆ እንዲያደርግ ተጠይቋል።
ከሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞም የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ ባለሀብቱ በገንዘብ፣ በእውቀት እና በቻለው መጠን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል የገባ ሲሆን ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን ድጋፍም ገልጿል።
ክብር ለሀገራቸው አንድነት እና አብሮነት ለተሰዋው የጀግናው መከላከያ ሰራዊት አባላት በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ላይ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ ተገኝተዋል።
(በትዕግስት ዘላለም)