ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የታቦት ማደሪያ ስፍራ አፀዱ

                     ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የታቦት ማደሪያ ስፍራ አፀዱ።

ምክትል ከንቲባዋ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኝ የታቦት ማደሪያ ከተለያዩ እምነት ተከታይ አባቶችና ምእመናን ጋር በመሆን ፅዳት አከናውነዋል።

ፅዳቱን ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አካባቢ በመገኘት ያከናወኑ ሲሆን፣ “የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር ማህበራዊ ጥቅሙም ትልቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያዊያን ህብር የሚገለፅበት ልዩ ድምቀት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባዋ፣ የጋራ የፅዳት መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ኃይማኖት፣ ብሄርና ማንነት ቢኖራቸውም አንድ መሆናቸውን ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።

የኃይማኖት አባቶቹም በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት “ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም በጋራ መስራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን” ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሰላምና ደህንነት ከመቸውም ጊዜ በላይ በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡