ኅዳር 19 /2015 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢስዋቲኒ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ላሳየችው መርህን መሰረት ያደረገ ጠንካራና ሚዛናዊ አቋም አድናቆታቸውን ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢስዋቲኒ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቱሊሲል ድላድላ ጋር የተወያዩ ሲሆን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና በፕሪቶሪያ ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ገለጻ አድርገዋል።
የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው ሀገሪቱ ለዘላቂ ሰላም ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ፈተና በገጠማት ወቅት ኢስዋቲኒ ላሳየችው መርህን መሰረት ያደረገ ጠንካራና ሚዛናዊ አቋም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢስዋቲኒ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው በተደረሰው የሰላም ስምምነት የኢስዋቲኒ መንግስት የተሰማውን ደስታ ገልጸው ለስምምነቱ ስኬታማ ተግባራዊነት አገራቸው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የኢስዋቲኒ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ቦታ እንደምትሰጠው የገለጹት ሚኒስትሯ ለጋራ ጥቅም ግንኙነቱ ወደ አዲስ ከፍታ ማሸጋገር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ በኢትዮጵያ እና በኢስዋቲኒ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ወዳጅነት እና ስትራቴጂካዊ የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW