በክልሉ የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቋመ

ኅዳር 19 /2015 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል የሙስና ወንጀልን ለመከላከል እና የወንጀሉን ተዋንያን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ክልላዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

ይህም በተለያዩ መዋቅሮች በተደራጀ መልኩ የሚፈፀም የመሬት ነክ ሙስና፣ ከግብር፣ ከግዥ፣ ለፕሮጀክቶች፣ ከግንባታ ፍቃድ፣ ከመንጃ ፍቃድ ሕገ ወጥ ንግድ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ለመንግስታዊ አገልግሎቶች ከዜጎች የሚጠየቅ ጉቦ፣ በፍትህ እና ሌሎችም ዘርፎች የሚፈፀም ሙስናን በመከላከል ወንጀለኞች ለሕግ ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው።

የተቋቋመውና አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴው በሙስና ወንጀል ላይ የሚያደርገውን የህግ ማስከበር ዘመቻ የሚያስተባብር፣ የወንጀሉን ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ነው።

ይህ የፀረ ሙስና ክልላዊ ኮሚቴ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት እንዲችል የህብረተሰቡ ሙሉ ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው መባሉን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡