ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ እንዲደረግበት ጥሪ አቀረቡ


መስከረም 9/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ እንዲደረግበት ጥሪ አቀረቡ።

በኒውዮርክ ከተማ እየተካሄደ ከሚገኘው 78ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ዘላቂ የልማት ግቦች የመሪዎች የፖለቲካ ፎረም ትናንትና ከትናንት በስቲያ ተካሄዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የዘላቂ ልማት ግቦችና እ.አ.አ በ2015 በአዲስ አበባ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ስምምነት ላይ የተደረሰበት የአዲስ አበባ የተግባር አጀንዳ ሰነድ ትግበራ የአፈጻጸም ጉድለት እንዳለበት ገልጸዋል።

ለዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ የአገር ውስጥ የሀብት ማሰባሰብ ጥረቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደረ አመልክተዋል።

በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት እየተደረገ ያለው የልማት ፋይናንስ በቂ ያልሆነና ፍትሐዊነት የጎደለው ነውም ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓቱ ማሻሻያና ለውጥ ያስፈልገዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራትና ተቋማት የእዳ ስረዛ ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱም አሳስበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።