ምግቦች እና የመጠቀሚያ ጊዜ መግለጫዎች


ምግቦች እና የመጠቀሚያ ጊዜ መግለጫዎች

በቴዎድሮስ ሳህለ

ግንቦት 24/2015 (ዋልታ) ለገበያ የሚቀርቡ በሙሉ ወይም በከፊል የተዘጋጁ ምግቦች በማሸጊያቸው ላይ ለተጠቃሚዎች የተለያዩ መረጃዎችን ያሰፍራሉ፡፡ ከነዚህ መረጃዎች ውስጥ ምግብ ሲዘጋጅ በግብዓትንት የተካተቱ ነገሮች፣ በምን ሁኔታ እና ለምን ያህል ጊዜ መቀመጥ እንደሚችሉ የሚገልጹ መረጃዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የዛሬ የጤና ደጉ አምዳችን በመጠቀሚያ ጊዜ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡ ለመሆኑ የታሸጉ ምግብ እና ምግብ ነክ ነገሮችን ስንገዛ የመጠቀሚያ ጊዜን ስንቶቻችን አይተን እና አረጋግጠን እንገዛለን? የመጠቀሚያ ጊዜን በተመለከተ ያሉ ልዩ ልዩ አገላለጾችን እና መልዕክታቸውንስ በሚገባ እንገነዘብ ይሆን? የትኞቹ አገላለጾች እና መረጃዎች የትኞቹን የምግብ ዓይቶች ይመለከታል በሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እንዳስሳልን፡፡

ምግብ ለሰው ልጆች እንደ መጠለያ እና ልብስ ሁሉ መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ያለ ምግብ መኖር አይቻልም፡፡ እንዲያውም ከመጠለያ እና ልብስም በላይ ቀዳሚው የሰው ልጅ ህልውና መሰረት ምግብ ነው ቢባል የሚያከራክር አይመስለም፡፡

ምግብ ቁልፍ የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎት ቢሆንም ከእሱ ጋር በተያያዘ በዓመት ከ600 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለህመም ሲዳረጉ ከ420 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በምግብ መመረዝ እና ተያያዥ መንስኤዎች ህይወታቸውን ያጣሉ ይላል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ፡፡
ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል የተዘጋጁ ምግቦች የመጠቀሚያ ጊዜ ገደብ አላቸው፡፡ የጊዜ ገደቡ ካለፈ ለጤና ጉዳት ከማድረሳቸውም በላይ እስከ ሞት የሚደርስ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ከመጠቀሚያ ጊዜ ጋር በተያያዘ ብዙዎቻችን የጠራ መረጃ ላይኖረን ይችላል፡፡ በተለምዶ የመጠቀሚያ ጊዜው አልፏል፣ ኤክስፓይርድ አድርጓል ወዘተ ሲባል እንሰማለን፡፡ ለመሆኑ እነዚህ እና ሌሎች አገላለጾች ትክክለኛ መልዕክታቸው ምንድነው?

መድኃኒት፣ ኬሚካሎች እና ምግቦች (ማርን ሳይጨምር) መጠቀሚያ ጊዜ አላቸው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል የተዘጋጁ ምግቦች የመጠቀሚያ ጊዜን በተመለከተ የተለያዩ አገላለጾች እና አጠቃቀምን ገላጭ መመሪያዎች መኖራቸውን ስንቶቻችን እናውቃለን? በምርቱ በተገለጸው ጊዜ ውስጥ ለሽያጭ የሚቀመጥ (Sell-By Date)፣ ምርቱን ከተገለጸው ጊዜ በፊት መጠቀም የተሻለ ነው (Best if Used By/Before)፣ ምርቱን በተገለጸው ቀን ይጠቀሙ (Use-By Date) እና የመጠቀሚያ ጊዜው ማብቂያ (Expiration Date) የሚባሉ መመሪያዎች በምግቦች ማሸጊያ ላይ አሉ፡፡ በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡

1ኛ ምርቱ በተገለጸው ጊዜ ውስጥ ለሽያጭ የሚቀመጥ (Sell-By Date)
በማቀዝቀዣ ውስጥ የሚቀመጡ እንደ እርጎ እና ክሬም የመሳሰሉ የወተት ውጤቶች በመሸጫ መደርደሪያ ላይ መቆየት የሚገባቸውን ጊዜ ለመግለፅ (Sell-By Date) የሚል ጽሑፍ ይለጠፍባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ምርቶቹ በመደርደሪያ ላይ መቆየት የሚችሉት እስከተለጠፈው ቀን ድረስ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ቀኑ ከደረሰ፣ ሻጮች ምርቶቻቸውን ከመደርደሪያ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጽሑፉ የምርቶቹን ደህንነት ላያሳይ ይችላል፡፡
ለምሳሌ የወተት ተዋፅኦዎች የመሸጫ ቀናቸው አልፎም እስከ አንድ ሳምንት ድረስ መጠቀም ጉዳት ላያደርሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው ምርቶቹ በተገቢው ቦታ እና ሁኔታ ሲቀመጡ እና ሲያዙ ነው፡፡

2ኛ. ምርቱን ከተገለጸው ጊዜ በፊት መጠቀም የተሻለ ነው (Best if Used By/Before)
ምርቱን ከተገለጸው ጊዜ በፊት መጠቀም የተሻለ ነው የሚለው መግለጫ የሚያመለክተው ምግቡ ትክክለኛ እና የተፈጥሮ ጣዕሙን ልናገኘው የምንችልበት በዚህ በተገለጸው የጊዜ ገደብ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ መልዕክት የመሸጫን ጊዜ ወይም የምርቱን ደህንነት/ጤናማነት ቀን የሚያሳይ አይደለም፡፡

3ኛ. ምርቱን በተገለጸው ቀን ይጠቀሙ (Use-By Date)
በተገለጸው ቀን ይጠቀሙ (Use-By Date) የሚል መልዕክት የሰፈረባቸው የምግብ ማሸጊዎች የሚያመለክቱት ምርቶቹ ከፍተኛ ጥራት በሚኖራቸው ጊዜ እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚመከርበትን የመጨረሻ ቀንን ያመለክታል። ስጋ፣ አሳ፣ ድብልቅ ሰላጣ፣ የፍራፍሬ ጭማቂዎች፣ ለመመገብ ዝግጁ የሆኑ ምግቦች በዚህ ጎራ ይካተታሉ፡፡ እነዚህ ምግቦች በቀላሉ የሚበላሹ እና በጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡

4ኛ. የመጠቀሚያ ጊዜው ማብቂያ ቀን (Expiration Date)
የመጠቀሚያ ጊዜ ማብቂያ በምግቦች ላይ የሚለጠፈው ምርቱ በተጠቀሰው ቀን አገልግቱ ያበቃል ወይም ምርቱን ከተጠቀሰው ቀን በኋላ አትጠቀሙ የሚል ነው፡፡ የህፃናት ፎርሙላ እና ምግቦች፣ ቫይታሚኖች፣ የኬክ ድብልቆች፣ የዳቦ እርሾ ወዘተ የመጠቀሚያ ጊዜ ማብቂያ የሚለጠፍባቸው ምርቶች ናቸው፡፡

በዚህ ከተሜነት እየተስፋፋ በመጣበት ወቅት በአብዛኛው ምግቦቻችንን ከገበያ ማዕከላት የሚሸመቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱት የመጠቀሚያ ጊዜ እና ተያያዥ መረጃዎችን በሚገባ መገንዘብ ይገባናል፡፡
ሰላም ቆዩ!