ም/ቤቱ የወንጀል ስነስርአት እና የማስረጃ ህግን በተመለከተው ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አደረገ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በወንጀል ስነስርአት እና የማስረጃ ረቂቅ ህግ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በ1952 ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ ውሎ በ1996 ተሻሽሎ የወጣው የወንጀል ስነ-ስርአት እና የማስረጃ ህግ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን ያግዛል የተባለው ይህ አዋጅ፣ በቋሚ ኮሚቴው ከህግ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክቶሬት እንዲሁም ከምክር ቤት በተደረጉ ጥናቶች መሰረት በተወጣጡ ጥያቄዎች ውይይት ተደርጎበታል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ማርቀቅ እና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት አቶ በላይሁን ይርጋ አዲሱ ረቂቅ የህግ ስነ-ስርአት ከዚህ ቀደም የነበረውን የአሰራር ሂደት ያሳልጠዋል ብለዋል።
የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የህግ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፍትህ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ጎዴቦ በበኩላቸው፣ ይህ ረቂቅ አዋጅ በተለያዩ መድረኮች ውይይት ከተደረገበት በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ ይፀድቃል ብለዋል።

(በቁምነገር አህመድ)