ም/ጠ/ሚኒስትሩ የሀገር ህልውናን ለማስጠበቅ የፖሊስ አባላትና አመራሮች ከፍተኛ ድርሻ ማበርከታቸውን ገለጹ

ግንቦት 26/2014 (ዋልታ) “የሀገር ህልውናን ለማስጠበቅ በተከናወኑ ተግባራት የፖሊስ አባላትና አመራሮች ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከፌዴራል ፖሊስ በስራ አፈፃፀማቸው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ እና በትምህርት ዝግጅታቸው ብቁ ለሆኑ ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች የማዕረግ እድገት ተሰጥቷል።

በዛሬው ዕለት በፌዴራል ፖሊስ አዳራሽ በተካሄደው የማዕረግ ማልበስ ስነ-ስርዓት ሦስት ሴቶች የረዳት ኮሚሽነር ማዕረግ አግኝተዋል።

በማዕረግ ማልበስ ስነ-ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባደረጉት ንግግር በሀገሪቱ የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ የፖሊስ ተቋምን ለማዘመን እና የማስፈፀም አቅሙን ለማጎልበት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙን እንደ አዲስ ለማደራጀት እየተሰሩ ባሉ ስራዎች በተለይ ደግሞ የሀገር ህልውና እና የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ በተከናወኑ ተግባራት የፖሊስ አባላት እና አመራሮች ከፍተኛ ድርሻ በማበርከታቸው አበረታች ውጤት መመዝገቡን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልፀዋል።

የፀጥታ አካላት በአሁኑ ወቅት የውጭና የውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሀገራችንን ለመበታተን እየሰሩ መሆኑን ተገንዝበው ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ በመሆን ኃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።

ከፍተኛ የፖሊስ ማዕረግን ለማግኘት በተግባር ተፈትኖ ማለፍን ይጠይቃል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፤ ለፖሊስ መኮንኖች እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን መግለፃቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።