ም/ጠ/ሚ/ር ደመቀ መኮንን የአድዋ ድል ሁሌም በከፍታ የሚዘከር የድል ወረታችን ነው አሉ

የካቲት 23/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በትውልድ ቅብብሎሽ ከተመዘገቡት ቱባ የታሪክ አብነቶች መካከል የአድዋ ድል በዓል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ታላቅ ማሳያ ሲሆን በቀደመው፣ በአሁኑ እና በሚቀጥለው ዘመን በከፍታ የሚዘከር የድል ወረታችን ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ለ126ኛው የአድዋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በረጅሙ የታሪክ ጉዞ በርካታ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች በሃገራችን ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍተው ሉዓላዊነቷን እና ነፃነቷን መዳፈራቸው በግልፅ ይታወቃል ብለዋል።

በዘመን ሰንሰለት ሃገራችን በውስጥ እና በውጭ ጠላቶች የተቃጡባትን የጦርነት ጥቃት ተከትሎ፤ ድፍረትን በሚጠየፉ ጀግና ልጆቿ ፈታኝ አውዶች በድል እየተሻገረች እነሆ በክብር ዘልቃለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፥ ኢትዮጵያ በክብር የመዝለቋ አመክንዮ በዜጎቿ አንድነት እና ህብረት ጥንካሬ ላይ እንደተመሰረተ አያሌ ቱባ የታሪክ አብነቶችን  ለማሳያነት በኩራት መምዘዝ እንደሚቻል ገልጸዋል።

በትውልድ ቅብብሎሽ ከተመዘገቡት ቱባ የታሪክ አብነቶች መካከል የአድዋ ድል በዓል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ታላቅ ማሳያ ሲሆን ፥ በቀደመው፣ በአሁኑ እና በሚቀጥለው ዘመን በከፍታ የሚዘከር የድል ወረታችን ነውም ብለዋል።

የአድዋ ድል በዓል ትናንትን በፅናት፤ ዛሬን በወኔ እንዲሁም ነገን በቁርጠኝነት የሃገራችን ሉዓላዊነት እና ነፃነት ሳይሸራረፍ በክብር እንድትዘልቅ በትውልድ ልቦና የድል አድራጊነት መንፈስ የሚያጋባ የወል እሴታችን ነው ሲሉም በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

የአድዋ ድል በዓል የሃገር ልዑዓላዊነት እና ነፃነት የማስከበር ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ምድር ተሻግሮ፤ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት መከበር ለፈጠረው ንቅናቄ የድል አድራጊነት ውሃልክ ያሰመረ ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ ጭምር እንደሆነም አንስተዋል።

በእኛ ዘመን እና ትውልድ ሃገራችን ልዑዓላዊነቷን ከሚዳፈሩ እና ነፃነቷን ከሚፈታተኑ ሃይሎች የተቃጡ መልከ-ብዙ ጥቃቶችን በጋራ በመመከት አንድነቷን ጠብቃ ጉዞዋን ወደፊት ቀጥላለችም ነው ያሉት።

በዘመናችን ሃገራችን የገጠሟትን ከባድ እና ውስብስብ ጥቃቶችን መመከት የተቻለበት ምስጢር ከቀደሙ አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ለአሸናፊነት ያበቃቸውን ወኔ በመውረስ እንዲሁም አንድነታችንን አጥብቀን እና ጠብቀን መጓዝ በመቻላችን ነውም ሲሉ አክለዋል።

አሁንም ቢሆን በሃገር ልዑዓላዊነት እና ነፃነት ዙሪያ የሚቃጡብንን ጥቃቶች በፅኑ አንድነት እየመከትን፤ በዕድገት ጉዞ ከፊትለፊት የሚጠብቁንን ውስብስብ ፈተናዎች እንድንሻገር ህብረታዊ የድል ልምምዳችንን በተግባር እንድናረጋግጥ አደራ ብለዋል።