ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነኝ አለች

የካቲት 8/2014 (ዋልታ) ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገባችበትን ውጥረት ለመፍታት ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች፡፡

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ሩሲያ ለአሜሪካ እና ኔቶ የደኅንነት ዋስትናዎች የሰጡትን ምላሽ በመጥቀስ ድርድር እና ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን በመከተል ችግሮችን እንፈታለን ማለታቸውን የክሪምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ገልፀዋል፡፡

ዩክሬን የችግሩ አንድ አካል ናት፤ ይህም ለሩሲያ የደኅንነት ዋስትናዎች ትልቅ ችግር በመሆኑ ፕሬዝዳንት ፑቲን ለመደራደር ፈቃደኛ ናቸው ማለታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን ሩሲያ በመጪው ረቡዕ ዩክሬንን ለመውረር ተዘጋጅታለች በሚል የሚያሰራጩትን መረጃ በመኮነን ዕለቱን የአንድነት ቀን እናደርገዋለን ሲሉ ዩክሬናዊያንን አረጋግተዋል፡፡

ሩሲያ ከኔቶ አባልነት ራሷን በማግለልና የጥምር ጦሩን ወደ ምስራቅ የመስፋፋት ፍላጎት በመንቀፍ ዩክሬን ሩሲያ ላይ ለሚፈጠረው የደኅንነት ስጋት መጠቀሚያ መሆን እንደሌለባት በተደጋጋሚ ስታስጠነቅቅ ከርማለች። በአንፃሩ እነአሜሪካ ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው በሚል እየወቀሱ ነው።

ዩክሬን በጉዳዩ ላይ ከሩሲያና ከቁልፍ የአውሮፓ ኅብረት አባላት ጋር ውይይት ለማድረግ ቀደም ሲል ጥሪ ማቅረቧ ይታወሳል፡፡