መጋቢት 1/2014 (ዋልታ) በብልጽግና የስልጣን ዘመን የሞግዚት አስተዳደር ቀርቷል፤ ሁሉም ክልል ስለራሱና ስለአገሩ ጉዳይ በነጻነት እየወሰነ በማስተዳደር ላይ ይገኛል ሲሉ የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ የቅድመ ጉባኤ ውይይት ላይ እየተካፈሉ የሚገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ በአሸባሪው የሕወሓት አስተዳደር ዘመን በክልሎች ላይ ተንሰራፍቶ የነበረው የሞግዚት አስተዳደር አሁን ላይ ቀርቷል ብለዋል።
በብልጽግና የስልጣን ዘመን ሁሉም ክልል በራሱ ሰውና በራሱ አዕምሮ እንዲመራ ነፃነት ተሰጥቶታል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
በአሸባሪው ሕወሓት ዘመን ክልሎች ከአንድ ማዕከል በሚተላለፍ መመሪያ ይተዳደሩ እንደነበር በመግለጽ አሁን በብልጽግና ዘመን ይህ ህገወጥ አሰራር መቀየሩን አስታውቀዋል።
የሕዝቦች ምሬትና የለውጥ ፍላጎት የወለደው ብልጽግና በአንድ ማዕከል የሚመራ አሰራርን ሳይሆን ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ አሰራር እየተከተለ ነው ብለዋል።
ለውጡ ያመጣው ብልጽግና ፓርቲ አሳታፊ በሆነ መንገድ እየሰራ በመሆኑ ማንኛውም ብቃት ያለው ኢትዮጵያዊ በጸጥታና ደኅንነት መዋቅሩ ውስጥ አገሩን እንዲያገለግል ዕድል ተፈጥሮለታል ሲሉም ተናግረዋል።