ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የኢሬቻ በዓል በየዓመቱ እየጎለበተ መጥቶ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በዓል ሆኖ በማየቴ ታላቅ ደስታ ፈጥሮብኛል አሉ

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

መስከረም 25/2016 (አዲስ ዋልታ) የኦሮሞ ህዝብ ባህል የሆነው ኢሬቻ በየዓመቱ እየጎለበተ፣ እያማረበትና እያበበ መጥቶ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በዓል ሆኖ በማየቴ ታላቅ ደስታ ፈጥሮብኛል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው 5ኛው የኢሬቻ ፎረምና የኢሬቻ ዋዜማ መድረክ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ”ኢሬቻ የወንድማማችነት እና የአንድነት አርማ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጀው 5ኛው የኢሬቻ ፎረምና የኢሬቻ ዋዜማ ዝግጅት የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች፣ ከተለያዩ አከባቢዎችና ከተሞች እንዲሁም ከውጭ አገር የመጡ እንግዶች በተገኙበት ስለ ኢሬቻ ምንነት፣ የህዝቦችን ወንድማማችነትና አንድነት በማጠናከር ረገድ ያለውን ፋይዳ በመወያየት ተማምረናል ብለዋል።

በተዘጋጀው መርኃ ግብርም ሆነ በሆራ ፊንፊኔ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ መላው የኦሮሞ ህዝብና በዓሉን ለማክበር የሚመጡ ኢትዮጵያውያን በሰላምና በደስታ እንዲያሳልፉ እየተሰራ ላለው ስራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና መላው የከተማዋ ህዝቦች ላደረጉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም የኢሬቻ በዓልን ለማክበር በመንገድ ላይ ላሉና ለመጡት የሀገሪቱ ብሔር ብሄረሰቦች እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም የኢሬቻ በዓል እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡