በሰላም ሚኒስትር የህግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬአለም ሺባባው የተመራ የልዑካን ቡድን በአፋር ክልል ከተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
የልዑካን ቡድኑ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተውጣጡ የአመራርና የባለሙያዎች ቡድን ያካተተ ነው።
የልዑካን ቡድኑ በእስከአሁን ቆይታው ገዳማይቱ፣ እንድፎ እና አዳይቱ የሚገኙ የማህበረሰብ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት አካሂዷል።
ጉብኝቱ በሌሎች አካባቢዎችም የሚቀጥል ነው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የማህበረሰቡን ፍላጎቶች እና ችግሮች በተለይም በግጭቶች ዙሪያ መሬት ላይ ያሉ ችግሮችን በግልጽ በማንሳት ሀሳባቸውን በስፋት ገልጸዋል።
በአካባቢው የሚከሰት የሰላምና የጸጥታ ችግር ምላሽና መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባም ተሰምሮበታል።
በውይይቱ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደተናገሩት “ሀገራችንን ያስቸገራት የአመላካከት ችግር ነው፤ ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መብታቸው የሚከበርባትና ልጆቻችን ህልማቸውን እውን የሚያደርጉባት ሀገር ትሆናለች” ብለዋል።
ለዚህም ግጭቶች ሲፈጠሩ በጉልበት ሳይሆን በማስተዋል መንቀሳቀስና በስልጡን ምክክር ማመን ያስፈልጋል ብለዋል።
አያይዘውም የህግ ማስከበር ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ማህበረሰቡን ወክለው ላነሷቸው ጥያቄዎች ወ/ሮ ፍሬአለም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በአፋጣኝ በመምከር እና በመተጋገዝ ለችግሮቹ መፍትሄ እንደሚበጅላቸውም አሳውቀዋል።
በመጨረሻም በቀጠናው ጸጥታ በማስከበር ሂደት ሌተቀን እየደከሙ ላሉ የመከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ሁሉ ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።