የህዳሴ ግድብ ህልውናን ለመጠበቅ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል – የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ህልውና ለመጠበቅ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ላይ ሁሉም አካል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር አሳሰቡ።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2013 ዓ.ም የበጋ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እንዲሁም ያለፉትን ዓመታት የሥራ ክንውን እውቅና የሚሰጥበት የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመገንባት ባሻገር ለህልውናውም ማሰብ ተገቢ ነው ብለዋል።

ግድቡ በደለል እዳይሞላ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራን በጥራትና በስፋት ማካሄድ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

በእንቦጭ አረም ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀውን ጣና ሐይቅ ለመታደግ አረሙን ነቅሎ ማስወገድ ብቻ መፍትሄ ባለመሆኑ በደለል እዳይሞላ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በየአካባቢው ማከናወን ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር መለሰ መኮንን በዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የሚሳተፉ አካላት ሥራው ዘላቂ እዲሆን በባለቤትነት  ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል ሲል አብመድ ዘግቧል።