ሳኡዲ የምታስገነባው አዲስ ከተማ – “ኒዮም ሲቲ” (Neom City)

በረሃን ወደ ከተማነት የመቀየር ጥበብ ልንለው እንችላለን፡፡ ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ የሚፈጅ ውድ ሥራም ነው፡፡ ከገንዘቡ ባሻገር ብዙ እውቀቶች ፈሰውበታል፤ አዳዲስ ነገሮች ተዋውቀውበታል፡፡ ዓለምን እጅ በአፍ አስጭኗል…. “ኒዮም ሲቲ” (Neom City)

በሳውዲው ልዑል መሀመድ ቢን ሳልማን ይፋ የሆነው ይህ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በ2017 የተጀመረ ሲሆን በውስጡ አራት ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ እነሱም ዘ ላየን፣ ኦክሳገን፣ ትሮጄና እና ሲንዳላህ ይሰኛሉ፡፡ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍም እ.ኤ.አ በ2030 ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

እስቲ ለዛሬ የዚህ ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነውና ከቀናቶች በፊት ግንባታው የደረሰበትን ደረጃ ስለሚያሳየው ቪዲዮ የተለቀቀውን ዘ ላይን (The Line) ፕሮጀክት እንመልከት፡፡

እንደ ቀጭን መስመር ቀጥ ያለ ከተማ ነው፡፡ 170 ኪ.ሜ ይረዝማል፡፡ በጎን እና ጎን ታጥሮ 170 ኪ.ሜትር ቀጥ ብሎ የተሰመረ የከተማ መስመር፡፡ ወደ ጎን 200 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን እስከ 9 ሚሊየን የሚደርሱ ነዋሪዎችን መያዝ ይችላል ተብሏል፡፡

ከተማው በጎን እና ጎን ወደ ላይ በ500 ሜትር ከፍታ ታጥሯል፡፡ አጥር ሲባል ግን በግንብ ወይ በቆርቆሮ የተሰራ አይደለም፡፡ በመስታወት ነው፡፡ ከኒዮርኩ ኢምፓየር ስቴት ጋር የሚስተካከል፤ የፓሪሱን ኤፍል ታወር በ170 ሜትር የሚበልጥ ሰማይ ጠቀስ የመስታወት አጥር፡፡

ይህ አዲስ የከተማ ሞዴል ተፈጥሯዊ ለሆኑ ነገሮች ቅድሚያ የሚሰጥ ሲሆን መቶ በመቶ ታዳሽ ሀይልን ይጠቀማል፡፡ በመሆኑም ምንም አይነት የካርበን ልቀት አይኖርም፡፡

170 ኪሎ ሜትሩን በ20 ደቂቃ ብቻ ከጫፍ ጫፍ መመላለስ የሚችል ፈጣን የሆነ ትራንስፖርት ተሰርቶለታል፡፡ ከዚህ ትራንስፖርት ውጪ ሌላ የግል መኪናም ሆነ መጓጓዣ መጠቀም አይፈቀድም፡፡ የምን አየር መበከል ነው?

ሲጀመርም ነዋሪዎች ከቤት እንደወጡ ከሆስፒታል እስከ ትምህርት ቤት፣ ከሱፐር ማርኬት እስከ መዝናኛ ስፍራ የፈለጉትን አገልግሎት በ5 ደቂቃ ብቻ ለማግኘት እንዲያስችላቸው ይደረጋል፡፡ በ5 ደቂቃ የእግር መንገድ ብቻ ሁሉንም አገልግሎት ማግኘት ይቻላል፡፡

በዚህ ስፍራ አገልግሎት የሚሰጠው በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በበለፀጉ አሰራሮች ነው፡፡ ላዩ ክፍት የሆነ ሲሆን የቀኑን አየር ንብረት እየለካ ሞቃቱን ወደ ቅዝቃዜ ቅዝቃዜውን ወደ ሙቀት የሚቀይር ማሽን ተገጥሞለታል፡፡

ብቻ ይህ በአለም የዘመናዊነት ታሪክ ውስጥ የራሱን ቀለም አስቀምጦ ያልፋል የተባለለት ፕሮጀክት እውን ሳውዲ ጨርሳ ታስመርቀዋለች ወይ? የብዙዎች ጥያቄ ነው! #NEOM city #the_line_project

በሳሙኤል ሙሉጌታ