ስምምነቱን ተከትሎ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እየሆነ ነው – የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ

ኅዳር 1/2015 (ዋልታ) በፌዴራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እየሆነ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

በወልዲያ፣ ቆቦ እና አላማጣ እና ሌሎች አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስተባብር ቡድን እንደተዋቀረም አስታውቋል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ ሽሬን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንደተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የመልሶ ግንባታ ስራ እየተሰራ መሆኑን ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታዋ የመብራት ኃይልን ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል። በአላማጣ አካባቢም የኃይል ጥገና እየተደረገ መሆኑን ነው የገለፁት።

በአጠቃላይ በጦርነቱ ምክንያት ኃይል ሳያገኙ የነበሩ ከተሞች ኃይል ማግኘት እንደጀመሩ ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ በላሊበላ፣ ቆቦ እና አላማጣ አካባቢዎች የመብራት ኃይል ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የጥላቻ ንግግሮች እንዲቆሙ ለመገናኛ ብዙኃን መመሪያ ተዘጋጅቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ መመሪያው ሰላምን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ መገናኛ ብዙኃን መብትና ግዴታቸውን እንዲያከብሩ ያለመ ነው ብለዋል።

መመሪያ በህዝቦች መካከል መራራቅ እንዳይፈጠርና መሰረታዊ የሙያ መርሆዎችን እንዲያከብሩ የሚረዳ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበር የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታዋ በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ መድገም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በሱራፌል መንግስቴ