ሶማሊያ ከአሜሪካ ኩባንያ ጋር የተደረገውን የነዳጅ ምርት ስምምነት ሰረዘች

የካቲት 14/2014 (ዋልታ) የሶማሊያ ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ነዳጅ ፈልጎ እንዲያመርት ‘ኮስትላይን’ ከተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ሰረዙ፡፡

መሃመድ አብዱላሂ መሃመድ (ፋርማጆ) እና መሃመድ ሁሴን ሮብል ከትናንት በስቲያ [ቅዳሜ] በኩባንያው እና በአገሪቱ የፔትሮሊዬም ሚኒስቴር መካከል የተፈረመውን ስምምነት መሰረዛቸው ይፋ ሆኗል።

የፔትሮሊዬም ሚኒስትሩ አብዲረሽድ መሃመድ አሕመድ ምርቱን እኩል በመጋራት መርሃ ግብር በ7 የተለያዩ የባሕር ዳርቻዎች ነዳጅ ፈልጎ እንዲያመርት ከ‘ኮስትላይን’ ጋር መስማማታቸውን አስታውቀው ነበር፡፡

እንደአል አይን ዘገባ ስምምነቱ ከሕግ ውጭ የተደረገ ነው በሚል በአገሪቱ መሪዎች ተሰርዟል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ “በምርጫ ወቅት ከውጭ አካላት ጋር ምንም ዓይነት ስምምነቶች እንዳይደረጉ በፕሬዝዳንቱ ተፈርሞ የወጣውን አዋጅ ይጥሳል”ም ነው የተባለው፡፡