ቁልፍ የመሰረተ ልማት ተቋማትን ደኅንነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል- የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት

ነሐሴ 5/2015  (አዲስ ዋልታ) ቁልፍ የመሰረተ ልማት ተቋማትን ደኅንነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጥናት ባካሄደባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ጉልህ በሆኑ የተመረጡ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች በሚስተዋሉ የደኅንነት ስጋቶች ዙሪያ ባለድርሻ አካላትን በመጋበዝ የፓናል ውይይት አካሄዷል።

በአራት ቁልፍ የመሰረተ ልማቶች ላይ በተደረገው ጥናት፤ የተቋማቱን የደኅንነት አጠባበቅ ሚዛን፤ የአካል ምልከታ፤ ደኅንነት አስተዳደርና ከአካባቢ ማህበረሰብ ጋር ስላላቸው መስተጋብር ተፈትሿል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትልና ቁጥጥር አለመኖሩ፤በሰው ኃይል የተጠናከረ ጥበቃ አለማድረግ ፤የአካባቢው ማህበረሰብ የእኔነት ስሜት እንዲኖረው አለመስራት በጥናቱ ከተለዩ ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው።

ለተቋማቱ የሚደረግ የደኅንነት ጥበቃ ስራ ከሚደርሰው ሀገራዊ ጉዳት እና ካለባቸው ስጋት አንጻር የሚመጥን መሆን እንዳለበት ተመልክቷል።

በተለይ የተቋማቱ አካላዊ ጥበቃን በሰለጠነ የሰው ኃይል ማጠናከር እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም በጥናቱ ተጠቁሟል።

ቁልፍ መሰረተ ልማቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚኖረውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ስራዎች ላይ በማሳተፍ በማህበረሰቡ ዘንድ የእኔነት ስሜት መፍጠር እንደሚገባም ተገልጿል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በፓናል ውይይቱ ላይ እደተናገሩት፤ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በህግ የተሰጠውን ቁልፍ የመሰረተ ልማቶችን የስጋት ተጋላጭነት የመፈተሸና እርምቶችን የመስጠት ኃላፊነት መሰረት በማድረግ በተመረጡ ተቋማት ጥናት አድርጓል።

የጥናቱ ትኩረትም የተቋማቱ የደኅንነት ስጋት መጠን የሚያደርሰውን ሀገራዊ ጉዳት ያገናዘበ መሆኑ ያመለከቱት አቶ ሲሳይ፤ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የደኅንነት ስጋት በጥናቱ የተካተቱ ቁልፍ የመሰረተ ልማት ተቋማት ችግር ብቻ እዳልሆነ በመጠቆም፤ ወደፊት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ቁልፍ የመሰረተ ልማቶች ላይ ተመሳሳይ ጥናት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

አሁን ግን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በጥናቱ የተዳሰሱ የደኅንነት ጥበቃ ስራ ክፍተቶችን ተቋማቱ ማረማቸውን በቀጣይ በሚካሄደው የሱፐርቪዥን ስራ እደሚፈትሽ አመልክተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የፌዴራል ፖሊሲ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ እንደገለጹት የትኛውም አካባቢ ያለ የደኅንነት ስጋት የሚቀረፈው በፀጥታ አካላት ብቻ ሳይሆን የባለድርሻ አካላትን አሳትፎ በጋራ በመስራት መሆኑን አብራርተዋል።

ቢሆንም የፀጥታ አካላት የቁልፍ የመሰረተ ልማቶችን ደኅንነት ለመጠበቅ ትኩረት በመስጠት የሰው ኃይል ተመድቦ መስራቱን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በፓናል ውይይቱ የተሳተፉ የየተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች በሰጡት አስተያየት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊነት ወስዶ በተቋማቱ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በጥናት ማሳየቱ ለተቋሞቻቸው ደኅንነት ልዩ ጥበቃ እንዲያደርጉ ግንዛቤ የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ በፓናል ውይይቱ ኢትዮ-ቴልኮም፣ ኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን፣ ብሔራዊ ነዳጅ ዲፖ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊሲና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሐላፊዎችና አመራሮችን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡