ቋሚ ኮሚቴው በቀረቡ ሁለት ረቂቅ አዋጆች ላይ ከአስረጂዎች ጋር ተወያየ

ሰኔ 23/2013 (ዋልታ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር፣ ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በቀረቡ ሁለት ረቂቅ አዋጆች ላይ ከአስረጂዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

በረቂቅ አዋጆቹ አስፈላጊነትና በዓላማዎቻቸው ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የአፈ-ጉባዔው የህግ አማካሪ ዶ/ር ዘለቀ ተመስገን ሲሆኑ፣ ምክር ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ውል በመግባት ጥናቶችን እያስጠና መቆየቱን እና የሪፎርም አጀንዳዎችን በመቅረጽ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩትን ሁለት አዋጆች ምክር ቤቱ አሁን ከደረሰበት ተቋማዊ እድገት ጋር የማይጣጣሙ፣ በአሰራር ሂደት የገጠሙ ክፍተቶችን መፍታት የማይችሉ እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን የመብት ጥያቄዎች በተገቢው ፍጥነትና ሁኔታ መመለስ የማያስችሉ በመሆናቸው ማሻሻያ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው፣ በምክር ቤቱ ስልጣንና ተግባር እንዲሁም የምክር ቤቱን ጽህፈት ቤት ለማቋቋም በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ዙሪያ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወክለው ለመጡ አስረጂዎች አቅርበዋል፡፡
በረቂቅ አዋጆቹ ላይ ለትርጉም አጋላጭ የሆኑ ቃላትና ሐረጋት ተገቢ በሆኑ ገላጭና ጊዜ አመልካች በሆነ መልኩ እንዲቀመጡ እና መሻሻል አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦች እንዲሻሻሉም አቅጣጫ ማስቀመጡን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።