ሰኔ 23/2013 (ዋልታ) – በሀረሪ ክልል የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃግብር የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል፡፡
የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሁሉም ሰው ተፈጥሮ በለገሰችው በገንዘቡ፣ በጉልበቱ፣ በሙያውና በክህሎቱ ያለምንም ግዴታ በራስ ተነሳሽነት የሚፈጽመው የማገዝና የመደገፍ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሁሉም ሰው ካለው ነገር ላይ ለሌላው ወገን ማካፈል መሆኑን የገለጹት ርእሰ መስተዳደድሩ፣ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ መሰማራት ማለት በራስ መተማመንን ከመፍጠር ባሻገር የሕይወት ክህሎትም የሚዳብርበት ዋንኛው መንገድ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጠንከር ያለና የህብረተሰቡን ፍላጎት ምላሽ ሊሰጡ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመስራት የምንጀምርበት ወቅት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ወጣቱን በፖለቲካና ኢኮኖሚው ዘርፍ ማሳተፍ እንደሚገባ በመግለጽ ሀገራዊ ልማትንና የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው የወጣቶች የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃግብር ላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርና ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ቤት የማደስ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አሚና አብዱልከሪም በበኩላቸው፣ በዘንድሮው የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃግብር በ13 ዘርፎች የተለያዩ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
በመርሃግብሩም የችግኝ ተከላና የአቅመ ደካሞች ቤት የማደስ ተግባር እንደሚከናወን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡