ሚያዝያ 29/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል የሸዋል ኢድ በዓልን በተሳካ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ርዕሠ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡
ርዕሠ መሥተዳድሩ በዓሉን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በክልሉ የሸዋል ኢድ በዓል በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር ግብረሃይል ተቋቁሞ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዓሉ የሀረርን ባህል፣ ቅርስ፣ ታረክና እሴትን በሚያስተዋውቅና በሚገልፅ መልኩ የተለያዩ መርኃ ግብሮች እንደሚከናወኑ ጠቁመው በዋናነትም መቻቻልንና ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ዲያስፖራውን ባሳተፈ መልኩ በዓሉ መከበሩም በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ማነቃቃትና ዲያስፖራው በክልሉ መዋለ ንዋዩን ኢንቨስት እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የክልሉ ኅብረተሰብ የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡና በእንግዳ ተቀባይነት ስሜት በማስተናገድ ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የበዓሉ አከባበር በስኬት እንዲጠናቀቅም የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
ተስፋየ ሀይሉ (ከሀረር)