ሐምሌ 01/2013 (ዋልታ) – በህይወት ያለውን ሰው ገድለዋል ተብለው በሀሰተኛ ምስክሮች 20 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው ማረሚያ ቤት የነበሩት ወይዘሮ አዛለች ቤተ ነጻ ሆነው ዛሬ ከእስር መለቀቃቸው ተገለጸ።
በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ ከአምስት ዓመት በፊት በእንጀራ እናቷ ተገደለች የተባለችው ግለሰብ በህይወት መገኘቷንና ሆኖም ግለሰቧ መሞቷ በሀሰተኛ ምስክሮች ተረጋግጦ የእንጀራ እናቷ ወይዘሮ አዛለች ለ20 ዓመት እስር መዳረጓ ተጠቁሟል፡፡
ወይዘሮዋ ከእስር ነጻ ተብለው የተለቀቁት የአማራ ክልል አስተዳደር ምክር ቤት ከይቅርታ ቦርድ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በማጽደቁ እንደሆነ የሰሜን ሸዋ ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ አስታውቋል።
በመምሪያው የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ ኮማንደር ደበበ መኩሪያ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቧ በሃሰት ምስክር በተሰጠው ፍርድ ከአምስት ዓመታት በላይ በእስር አሳልፈዋል።
ግለሰቧ የእንጀራ ልጇን በመግደል ወንጀል በሃሰተኛ ምስክር እንደፈጸሙ ተደርጎ የ20 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት መቆየታቸውን አውስተዋል።
ይሁን እንጂ ሞተች የተባለችው ግለሰብ ከተሰወረበችበት አካባቢ ወደ ተወለደበች መንደር መመለሷን አመልክተዋል።
ይህን የሰሙትና ባልሰሩት ወንጀለኛ የተባሉት ግለሰብ ጉዳዩ በሃሰት የተፈጸመ መሆኑንና ግለሰቧ በህይወት መኖሯን በመጥቀስ ለሚመለከተው አካል ማመልከታቸውን ጠቅሰዋል።
ፖሊስም በቀረበው አቤቱታ መሰረት ተገደለች የተባለችው ግለሰብ በህይወት መኖሯን ከአካባቢው ነዋሪዎች በተገኘ ማስረጃ መሰረት ጉዳዩ ተጣርቶ ትክክለኛ መሆኑ አረጋግጧል ብለዋል።
በዚህም ለክልሉ የይቅርታ ቦርድ ጉዳያቸው ቀርቦ ተገቢው ውሳኔ እንዲያገኝ ጥረት ቢደረግም ከሶስት ወራት በላይ ሳይለቀቁ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ የአማራ ክልል አስተዳደር ምክር ቤት ከይቅርታ ቦርድ የቀረበለትን ይህንኑ ጉዳይ መርምሮ ከሰኔ 27/ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወይዘሮ አዛለች በይቅርታ እንዲፈቱ ወስኖ በደብዳቤ እንዳሳወቃቸው አስረድተዋል።
የውሳኔው ደብዳቤ ዘግይቶ ለደብረ ብርሃን ማረሚያ ቤት በመድረሱ ወይዘሮ አዛለች ቤተ ከሐምሌ 1/ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከእስር ነጻ ሆነው መውጣታቸውን አስታውቀዋል።
ግለሰቧ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ሲመለሱም የአካባቢው ነዋሪዎች ለኑሮ መቋቋሚያ የሚሆን የገንዘብና የመጠለያ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ኮማንደር ደበበ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በቦታው በመገኘት ባልፈጸሙት ወንጀል በእስር ቤት የኖሩትን ወይዘሮ አዛለች ቤተን በአካል አግኝቶ ባነጋገራቸው ወቅት “በሃሰት ምስክር በርካታ ንጹሃን ባልሰሩት ወንጀል እየማቀቁ ለመሆኑ እራሴ ማሳያ ነኝ” ብለዋል።
በዚህም ሀሰተኛ ምስክሮች በማህበረሰቡ እና በሀገር ላይ እያደረሱ ያለውን ጥፋት ለማስቆም መንግስት ወንጀል መርማሪዎች ላይ ትኩረት አደርጎ መስራት እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል።
ባልፈፀምኩት ወንጀል ከአምስት ዓመታት በላይ በማረሚያ በመኖሬ ምክንያት የተነጠቅኩትን የእርሻ መሬቴን መንግስት እንዲያስመልስልኝ እፈልጋለሁ፤ መኖሪያ ቤቴም በመፍረሱ መጠለያ እንዳገኝ ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል።
ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉም የሀሰተኛ ምስክር እያደረሰ ያለውን በደል በማስተማር ከፍትህ አካላት ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡም ወይዘሮ አዛለች ገልጸዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ ከአምስት ዓመት በፊት በእንጀራ እናቷ ተገደለች የተባለችው ግለሰብ በህይወት መገኘቷንና ሆኖም ግለሰቧ መሞቷ በሀሰተኛ ምስክሮች ተረጋግጦ የእንጀራ እናቷ ወይዘሮ አዛለች ለ20 ዓመት እስር መዳረጓን ኢዜአ ቀደም ብሎ መዘገቡን አስታውሷል።
የተከሰስኩበት ወንጀል ሃሰት መሆኑ ቢረጋገጥም ከእስር ልፈታ አልቻልኩም በማለት ወይዘሮ አዛለች ቅሬታ አቅርበው እንደነበርም ተመለክቷል።