የጎርጎራ ከተማ  መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ  ነው- ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

                                                  የጎርጎራ ከተማ  መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት

ሐምሌ 01/2013 (ዋልታ) – የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነውና የጎርጎራ ከተማን የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተጀመረው መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የመዋቅራዊ ፕላኑ ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ አየልኝ ተበጀ ለኢዜአ እንደገለጹት  የከተማው የመጀመሪው ዙር  የመዋቅራዊ ፕላን ረቂቅ ዝግጅት ተጠናቆ የመጨረሻው ዙር ስራ ተጀምሯል፡፡

መዋቅራዊ ፕላኑ ለከተማው የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ሀብቶች ጥበቃና ልማት እንዲሁም ለጣና ሀይቅ የውሃ ሀብቶች ደህንነትና ክብካቤ ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ጊዜ ተወስዶ በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በጎርጎራና አካባቢው የሚገኙ የጣና ሀይቅ ገዳማትና ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት ቅርሶቻቸው ተጠብቀው እንዲለሙና ለቱሪዝም ልማቱ ሰፊ አገልግሎት እንዲሰጡ በመዋቅራዊ ፕላኑ መካተታቸውን አመልክተዋል።

መዋቅራዊ ፕላኑ የከተማው ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል የሚያገኙባቸውን የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚስፋፉበትንና የሚለሙበትን አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሆኖ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቡድን መሪው አክለው መዋቅራዊ ፕላኑ ጎርጎራን ለነዋሪዎቿ ምቹና ጽዱ የመኖሪያ አካባቢ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላች የቱሪስቶች ማረፊያና መዝናኛ ስፍራ ለማድረግ በጥንቃቄ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ለመዋቅራዊ ፕላኑ የመጀመሪያው ዙር የረቂቅ ዝግጅት አስፈላጊ የሆኑ በቂ ግብአቶች ማሰባሰብ እንደተቻለ ጠቁመው ከህብረተሰቡና ከሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ መረጃዎች  እየተሰባሰቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መዋቅራዊ ፕላኑ ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት እንዲያገለግና የከተማዋን 7 ሺህ ሄክታር የቆዳ ስፋት የሚያካትት ሆኖ እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ጎንደር ዩንቨርሲቲ መዋቅራዊ ፕላኑን በሀምሌ ወር 2013 ዓም ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለጎርጎራ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት እንደሚያስረክብ ቡድን መሪው አስታውቀዋል፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው የመዋቅራዊ ፕላኑ ዝግጅት በዩንቨርሰቲው የምርምርና ማህበረሰብ ምክትል ፕሬዝዳንት የቅርብ አመራርና ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የጎርጎራ ከተማን የወደፊት እድገትና ልማት ትኩረት ባደረገው መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት የዩንቨርሲቲው የአርክቴክቸር ባለሙያዎችና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ትምህርት ክፍል መምህራን በዋናነት እየተሳተፉ መሆኑን አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግስት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጎርጎራ ከተማን መዋቅራዊ ፕላን በባለቤትነት እንዲያዘጋጅ ሃላፊነት የሰጠ ሲሆን፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲና የክልሉ የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት ደግሞ በስራው ላይ በአጋርነት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አህመድ በሀገር አቀፍ ደረጃ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በታቀፈችው የጎርጎራ ከተማ  በቅርቡ በመገኘት ግንባታውን በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡