በሀሰተኛ የብር ኖት ለመገበያየት የሞከረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

መጋቢት 26/2013 (ዋልታ) – በጉጂ ዞን አዶላ ከተማ በ9 ሺህ 400 ሀሰተኛ የብር ኖት ለመገበያየት የሞከረ ግለሰብን እጅ ከፍንጅ መያዙን ፖሊስ አሰታወቀ።

የከተማው ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን ካባ ነጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ግለሰቡ በያዘው ሀሰተኛ የብር ኖት ትላንት ከአንድ አርሶ አደር ከብት ለመግዛት በድርድር ላይ እንዳለ ከህዝብ በደረሰ ጥቆማ እጅ ከፍንጅ ተይዟል።

ግለሰቡ  ኪሱ ሲፈተሽ 47 ሀሰተኛ ባለ 200 የብር ኖት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አውሎ ተጨማሪ ሀሰተኛ የብር ኖት መኖር አለመኖሩን ለማጣራት ምርመራ  እያካሄደ መሆኑን ዋና ሳጂኑ ገልጸዋል፡፡

የሀሰተኛ ብር ኖት ዝውውር እየተስፋፋ በመምጣቱ ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳሰቡት ሳጅን ካባ፣ ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙት  ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በከተማው በህዳር 2013 ዓ.ም ብቻ 724 ባለ 100 እና 200 ሀሰተኛ የብር ኖት ይዘው ከብት ለመግዛት የሞከሩ ግለሰቦች በህዝብ ጥቆማ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን  አስታውሰዋል፡፡