በሀገሪቱ የሚታዩ የኢንቨስትመንት ማነቆዎች አፋጣኝ መፍትሄ ይሰጣቸዋል – አቶ ደመቀ መኮንን

ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) – በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የኢንቨስትመንት ማነቆዎች አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  መኮንን አሳስቡ።

በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም የተጠያቂነት ስርዓትን እስከታች ድረስ በማውረድ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ውጭ ኢንቨስተሮች የሚያጋጥማቸውን ማነቆዎች ለመፍታት የተቋቋመው ሀገራዊ የቅንጅት መድረክ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጽዮን ተክሉ በሀገራችን መዋለ ነዋያቸውን ያፈሰሱ ባላሃብቶች ስለሀገራችን ምን ይላሉ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ገለፃ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሺነር የሆኑት ለሊሴ ነሚ በበኩላቸው የድህረ ኢንቨስትመንት ክትትል ስትራቴጂ አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ የገመገመ ጽሁፍ አቅርበው በተነሱት ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጽዮን ተክሉ በመግለጫቸው ያለፈው ምርጫና በትግራይ ክልል የነበረው ህግ የማስከበር ዘመቻ፤ የብዙ ኢንቨስትሮች ስጋት ነበር ያሉ ሲሆን ፤ሆኖም ግን የጉዳዩን ኣሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሰላም ሚኒስቴር፤ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተሰራ የተቀናጀ ስራ ውጤታማ ተግባር ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

የኢፌዲሪ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ከክልሎች ጋር ያለው የቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት ዘርፉን እየጎዳው ያለ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ የሆኑት  አምባሳደር ግርማ ብሩ  በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ የሚታየው የማስፈፀም ችግሮች ዘርፉን እየጎዳው መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የአስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት የዘርፉን ጥቅም በሚገባ በመረዳት ማነቆዎችን ፈተው አፋጣኝ ለውጥ ማምጣጥ ይገባል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡