በሀገር ሉዓላዊነት አንደራደርም፤ ሃገርን ለማፈራረስ የሚጥሩ ሃይሎችን እንታገላቸዋለን- ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ሐምሌ 15/2013 (ዋልታ) – በሀገር ሉዓላዊነት አንደራደርም፤ ሃገርን ለማፈራረስ የሚጥሩ ሃይሎችን እንታገላቸዋለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመደገፍ እና የህወሃት ጁንታ ቡድንን እኩይ ተግባር ለመቃወም ከ1.5 ሚሊየን በላይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የተገኙበት ሰልፍ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

በሰልፉ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ፣ የከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት፣ አርበኞች፣ ወጣቶች፣ የሐይማኖት አባቶች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተገኝተዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሰልፉ ታዳሚዎች ባስተላለፉት መልዕክት ወትሮም ቢሆን ለትግራይ ህዝብ ደንታ የሌለው የሽብርተኛው የህወሃት ቡድን መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ ራሡን እንዲያይ እድል ቢሰጠውም ከእኩይ ተግባሩ ሊላቀቅ እንዳልቻለ ገልጸው፣ አሁንም የጥፋት ሃይሉን ተያይዞታል ብለዋል።

በሰልፉ ላይም የከተማዋ ነዋሪዎች የተለያዩ አሸባሪውን ህወሃት ጁንታ ቡድን የሚያወግዙ መፈክሮችን በመያዝ በመስቀል አደባባይ የተገኙ ሲሆን፣ ሠልፈኞቹ “ከጀግናው ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ነን፤ የህወሓት ጁንታ ቡድን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላት በመሆኑ በተባበረ ክንድ እናሸንፈዋለን” ሲሉ ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ እና ጉልበት እየተገነባ ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ የማንንም እርዳታ ሳንፈልግ እናጠናቅቀዋለን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ሴቶች ማህበር ተወካዮች በበኩላቸው፣ ህጻናትን እና ሴቶችን ለጦርነት እየማገደ ያለው ጅንታው ህወሃት ቡድን ከጥፋቱ እንዲታቀብ እናወግዛለን፤ ዓለምም ይህንን እኩይ ተግባሩን ሊያወግዘው ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።