በሃገር ሉዓላዊነትና ጥቅም ላይ የሚሰነዘሩ የውጭ ተጽዕኖዎችን በጋራ መከላከል ይገባል – የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ሰኔ 07/2013 (ዋልታ) የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት የፓርቲ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በሃገር ሉዓላዊነትና ጥቅም ላይ የሚሰነዘሩ የውጭ ሃይሎችን ተጽዕኖ ለመከላከል በጋራ እንዲሰሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

መንግስት ችግሩን ለመፍታትና የውጭ ኃይሎች እየፈጠሩ ያሉትን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመከላከል ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ እንዲሰራ ምክር ቤቱ በመግለጫው ጠይቋል።

6ኛው ሃገራዊ ምርጫ እስከሚካሔድበት እለት ድረስ በቀሩት ቀናት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የሚመለከታቸው የሰላምና ፀጥታ አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም መላው ህዝቡ ለሰላምና ጸጥታ መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

የሃገሪቱን የጸጥታ፣ የደህንነት እና የፍትህ አካላት ምርጫው በሰላም ተካሒዶ ይጠናቀቅ ዘንድ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በራቀ መልኩ ነጻና ገለልተኛ አገልግሎት እንዲሰጡ የጠየቀው መግለጫው፥ በምርጫው ሂደት የእጩዎችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ደህንነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንዲሰራም አመልክቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሒደት ላጋጠሟቸው ችግሮችና ለቦርዱ ላስገቡት ማመልከቻ ከምርጫው በፊት ምላሽ እንዲሰጥ በመጠየቅም በየአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በየአካባቢያቸው የጋራ ምክር ቤት በማቋቋምና በማጠናከር ያለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስቧል።

ምርጫው በትግራይ ባይካሔድም በክልሉ በተፈጠረው ችግር በህዝብ ላይ የደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ በአፋጣኝ እንዲቆም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና የፌዴራል መንግስት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቀው መግለጫው፤ የደረሰውን ሰብዓዊ ጉዳት በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ለፍትህ እንዲቀርብም አመልክቷል።

በጸጥታና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ምርጫ በማይካሔድባቸው አካባቢዎች ያሉ ችግሮች በአፋጣኝ ተወግደው ምርጫው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከመስከረም 30 በፊት እንዲካሔድ እንዲያደርግም ነው የጠየቀው፡፡

ከምርጫ ውጤት ይፋ መሆን ጋር በተያያዘም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎችም ህዝብን በማሳሳት ለግጭት እንዳያጋልጡ ሊጠነቀቁ ይገባል ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል፡