ግንቦት 06/2013 (ዋልታ) – የትምህርት ሚኒስቴር ራሳ ከተሰኘ የግል ኩባንያ ጋር በህንድ ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ።
የነፃ የትምህርት እድሉ ከአጫጭር ስልጠና እስከ ፒ ኤች ዲ የሚደርሱ ፕሮግራሞችን የያዘ ነው ተብሏል፡፡
ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ እና የራሳ ማኔጅመንት እና የማማከር ድርጅት ስራ አስኪያጅ ዶክተር ራጃሽ ሞሲስ መፈረማቸው ተጥቅሷል።
ሚኒስትር ዴኤታው የትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንን አቅም ለማሳደግ በሚያደገው ጥረት ውስጥ እንዲህ ያሉ የነፃ የትምህርት እድሎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ኩባንያው ከዚህ በፊት ከ1ሺ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በህንድ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች እና መስኮች ነፃ የትምህርት እድል ሲሰጥ መቆየቱ ተነስቷል፡፡
በቀጣይ ከ5ሺ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል እንደሚሰጥ የራሳ ማኔጅመንት ስራ አስኪያጅ ዶክተር ራጃ ሞሲስ መጥቀሳቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡