ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ የሚስተዋሉ አለመግባባቶች በአፍሪካዊ መፍትሄ ለአፍሪካ ችግሮች በሚለው ፓን-አፍሪካዊ መርህ ሊፈቱ እንደሚገባ ኬንያውያን ምሁራን ገለፀዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በኬንያ የዓለም ግንኙነቶች ምሁራን ማህበር ትብብር በበይነ መረብ የፓናል ውይይት አካሂደዋል፡፡
በኬንያ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ያለውን የትብብር መንፈስ ማጠናከርና የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት ለሁሉም የጋራ ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል፡፡
ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀም እንዲረጋገጥም ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንደሚገባቸው አምባሳደር መለስ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያውያን የማንንም ድጋፍ ሳይጠይቁ በራሳቸው ወጪ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መገንባታቸው አፍሪካውያን የራሳቸውን ፕሮጀክት በራሳቸው አቅደው እንደሚያሳኩ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱን አምባሳደሩ ጠቅሰው የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የቀጠናውን ሀገራት የኃይል እጥረት ከመፍታቱም ባለፈ የአፍሪካ ቀንድን የበለጠ የሚያሰተሳስርና በቀጠናው ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር የሚያሳድግ መሆኑንም አምባሳደር መለስ ገልፀዋል።
ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር እንዲመጣ ምሁራን የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኬንያ በሚገኘው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ (United States International University (USIU) የዓለም ግንኙነት ምሁር ዳን ኦዳባ በበኩላቸው፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለግብፅና ሱዳን ብሎም ሌሎች የቀጠናውን ሀገራት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ሁሉም ሀገራት ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።
የግድቡ መገንባት ለቀጠናው ሀገራት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን አጀንዳ 2063 እውን ለማድረግም ቀጠናዊ ውህደትን በማፋጠን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ገልፀዋል።
በውይይቱ ኬንያ የዓለም ግንኙነቶች ምሁራን ማህበር ሊቀ መንበርና በስትራትሞር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ፕሮሰፌር ዶ/ር ኪገን ሞሩምባሲ፣ የማህበሩ ምክትል ሊቀ መንበር ሌናርድ ወኛማ፣ በUSIU የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ዳን ኦዳባ ተሳትፈዋል።
በኬንያ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ሁለተኛ አማካሪና በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ እጩ የሆኑት አቶ ዘሩባቤል ጌታቸውም “Decolonizing the Nile” የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ማቅረባቸውን የኤምባሲው መረጃ አመላክቷል፡፡