የካቲት 30/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 50 ሺሕ ሊትር የምግብ ዘይት በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ ቡሽራ አሊዪ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት እየተባባሰ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በክልሉ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዘይት ዋጋ መናርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸው በዚህም በኮድ 3 ኢት 29490 ተሳቢ የጭነት መኪና ተጭኖ በህገወጥ መንገድ ሲዟዟር የነበረን 50 ሺሕ ሊትር የምግብ ዘይት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ በፖሊስ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንና አሽከርካሪው ለጊዜው መሰወሩን ጠቁመዋል።
በቁጥጥር ስር የዋለው የምግብ ዘይትም ለክልሉ ነዋሪ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚከፋፈል አመልክተው የክልሉ ነዋሪ የምግብ ዘይት ፍጆታን ለመሟላት ከንግድ ሚኒስቴርና ከሸማቾች ማኅበራት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ሲያደርገው እንደነበረው በቀጣይም የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ የሚያደርጉ ህገወጥ ነጋዴዎችን ማጋለጥና ከክልሉ መንግሥት ጋር በትብብር እንዲሰራ መጠየቃቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡