በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ወደ ሱዳን ሊወጡ የነበሩ 51 ሰዎች ተያዙ

ሐምሌ 04/2013 (ዋልታ) – በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውሃ ከተማ በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ወደ ሱዳን ሊሻገሩ የነበሩ 51 ግለሰቦችን ትናንት መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

ከተያዙት ውስጥ 48ቱ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።

የምእራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ወርቄ ጫኔ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ግለሰቦቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ A3-32469 (አአ) በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ እንዳሉ ተይዘዋል።

ግለሰቦቹን ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሁለት ደላሎችና የአይሱዙ ረዳት ጨምሮ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር  ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

የአይሱዙ አሽከርካሪው ለጊዜው በመሰወሩ ክትትል እየተደረበት መሆኑን አመልክተዋል።

አይሱዙ ተሽከርካሪው ሞተር ብስክሌት በሚያሽከረክሩ ሁለት ደላሎች መንገድ እየተመራ ይጓዝ እንደነበር የገለጹት ኃላፊዋ፤  የአይሱዙ አሽከርካሪውና ደላሎች በመካከላቸው  የተፈጠረ አለመግባባት ለመያዛቸው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዋና ኢንስፔክተር ወርቄ ገለጻ፣ የተያዙት ሰዎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ይደረጋል።

በህገወጥ መንገድ ከአገር ለመውጣት የነበሩት ሰዎች ለደላላና ለትራንስፖርት በአስር ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ መክፈላቸውን ገልጸዋል።