በህግ ከለላ ስር ላሉ ዜጎች ‘የዋስትና መብት’ ማረጋገጥ በሚል ለዳኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው

የጀስትስ ፎር ኦል ፕሬዝዳንት ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ

በህግ ከለላ ስር ላሉ ዜጎች ‘የዋስትና መብት’ ማረጋገጥ በሚል ከዞን፣ ከወረዳ፣ ከፍተኛ እንዲሁም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለተውጣጡ ዳኞች ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ነው።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ“ጄስትስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ” ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የፍትህ ስርዓትን ነፃ እና ገለልተኛ እንዲሆን የባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ነው ተብሏል።

ዳኞችና የህግ ባለሙያዎች ገለልተኛ በመሆን ፈጣን የሆነ የጉዳዮች ፍሰት እንዲኖር ብሎም ፍርድ ሳያገኙ በማረሚያ የሚጉላሉ ሰዎች እልባት እንዲያገኙ ያግዛልም ነው የተባለው።

የጀስትስ ፎር ኦል ፕሬዝዳንት ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ በኦሮሞ ባህል የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና ሀደሲንቄዎች ሰላምና እርቅን በማስፈን በዳኝነት አሰጣጥ ያሉትን እሴቶች ጠብቆ በማቆየቱ የፍትህ ስርዓት በግብዓትነት መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

ስልጠናው በቀጣይ ሰላምን ማስፈን፣ የህግ የበላይነትን ማስከበር እንዲሁም በምርጫ ወቅት ምን አይነት የፍትህ አሰጣጥ ሊኖር ይገባል? በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ለሁለት ቀን ይቀጥላል።

ከጀስትስ ፎር ኦል ላለፉት 28 አመታት በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቱ እንዲሻሻል ሲሰራ መቆየቱም ተገልጿል።

(በሀኒ አበበ)